በአማራ ክልል ከወራሪው ኃይል ነፃ በወጡ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ለመደገፍና ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የድጋፍ ጥሪ ቀረበ

60

ባህር ዳር፣ ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ከወራሪው ህወሓት ነፃ በወጡ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ለመደገፍና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ።

ኮሚሽነር ዘላለም ልጅዓለም ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በዶክተር ዐቢይ አህመድ የግንባር አመራር በተካሄደ ዘመቻ ነፃ በወጡ አካባቢዎች ተፈናቃዮችን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደቀዬአቸው ለመመለስ እየተሰራ ነው።

የተፈናቃዮችን የትራንስፖርት ወጭን ጨምሮ የምግብ፣ የሕክምናና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ኮሚሽኑ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ጭፍጨፋና ዝርፊያ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ነባራዊውን ሁኔታ እንዲቀበሉ የስነልቦና ትምህርት የሚሰጣቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በወረራ ውስጥ ሲኖሩ ለነበሩ ከ7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በምግብና በመድሐኒት እጥረት ችግር ውስጥ በመቆየታቸው ተከታታይ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።

እንደ ኮሚሽነር ዘላለም ገለጻ፤ በወረራ ውስጥ ለነበረው ህዝብ ለወር ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የምግብ እህል እንዲሁም የአልባሳት፣ የማብሰያና ሌሎች ቁሳቁስ ድጋፍ ያስፈልጋል።

ድጋፉን ለማሟላትም መንግስት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የውጭና የውስጥ ግብረሰናይ ድርጅቶችና ዳያስፖራዎች የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚሽነር ዘላለም እንዳሉት የተፈናቀሉና በወረራ ውስጥ የነበሩ 9 ሚሊዮን ዜጎችን ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስና መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ሃብት ለማሰባሰብ መንግሥታዊ ዕውቅና ያለው አሰራር ይዘረጋል።

ይህም ከዚህ በፊት በተናጠል በመንቀሳቀስና ካለመናበብ ጋር ተያይዞ የተከሰተውን የሃብት ብክነትና ኢ-ፍትሐዊነትን በሚያስወግድ መልኩ ሀብት ለማሰባሰብ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በመንግስት እውቅና የሚከናወነው የሀብት አሰባሰብ ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ፍትሐዊነትን የሚያሰፍን በመሆኑ የሚደግፉ አካላት በዚህ አሰራር መሰረት ድጋፍ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።

አሸባሪው ህወሓት ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በጅምላና በተናጠል ከጨፈጨፋቸው ውጭ በምግብና በሕክምና እጥረት በርካታ ሴቶች፣ ህጻናትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል።

በአንጻሩ ወደ አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ሸሽተው ለተፈናቀሉ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የምግብና የሕክምና ድጋፍ ማድረግ በመቻሉ የሰው ህይወት እንዳላለፈ ኮሚሽነር ዘላለም ተናግረዋል። 

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም