በአካባቢ የጸጥታ ጥበቃና ህብረተሰቡን በማነቃቃት ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው --የቀድሞ ሠራዊት አባላት

31

ሚዛን አማን ፣ታህሳስ 2/2014 (ኢዜአ) ለሀገር ማዳን ዘመቻው ስኬት በአካባቢ የጸጥታ ጥበቃና ህብረተሰቡን በማነቃቃት ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው ሲሉ በቤንች ሸኮ ዞን የቀድሞ ጦር ሠራዊት አባላት ገለጹ።
 

የቀድሞ ሠራዊት አባላቱ የአካባቢያቸው ሰላም በአሸባሪው ህወሓት ተላላኪዎች እንዳይደፈርስ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ነቅተው እየጠበቁ መሆኑንም ለኢዜአ ገልጸዋል።

በቤንች ሸኮ ዞን የደቡብ ቤንች ወረዳ ነዋሪ ሃምሳ አለቃ ጣዕሜ ተስፋዬ እንዳሉት መከላከያ ሠራዊቱ አገርን ለማስቀጠል የማይተካ ህይወቱን በመስጠት ዋጋ እየከፈለ ነው።

በጦር ጉዳት ዳግም ለመዝመት ባለመቻላቸው ቢቆጩም ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት ህብረተሰቡ በስንቅና በሞራል የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲቀጥል እያበረታቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የህዝቡ ተነሳሽነት እንደሚደነቅ የገለጹት ሃምሳ አለቃ ጣዕሜ፣ በአካባቢያቸው ወጣቱ እንዲዘምት፣ መዝመት የማይችል በስንቅና ሞራል ድጋፉን እንዲያጠናክር እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

በስንቅ ዝግጅትና በአካባቢ ጥበቃ ግንባሮች ተሰልፈው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የገለጹት ሃምሳ አለቃ ጣዕሜ፣ የደጀንነት ተግባር ሠራዊቱን እንደሚያነቃቃ ገልጸዋል።

ለወታደር የህዝቡ ደጀንነት ብርታት መሆኑን በተግባር እንደሚያውቁት ገልጸው፣ የህዝቡ የደጀንነት ሥራ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የአሸባሪውን የውንብድና ሥራ በፊትም ጠንቅቀው እንደሚያውቁ የገለጹት ሃምሳ አለቃ ጣዕሜ፣ "ህወሓት ቀድሞም የሀሰት ፕሮፓጋንዳ አለቃ እንጂ የጦር ወኔም ልብም የለውም" ሲሉ አሸባሪውን ገልጸውታል።

ወጣቱ ትውልድ አንድነቱን በማጠናከር እንደ ጀግኖች አባቶች የአገሩን ክብርና ሉአላዊነት ጠብቆ በማቆየት በታሪክ የሚታወስ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሌላው የቀድሞ ሠራዊት አባል አስር አለቃ መሸሻ ካሳ በበኩላቸው ከመንግስት ጎን ተሰልፈው ለሠራዊቱ የደጀንነት ሥራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ሁሉም ሰው በግንባር መሰለፍ ባይጠበቅበትም አካባቢን በማልማት፣ ከሰርጎ ገቦች በመጠበቅ እና ስንቅ በማዘጋጀት በሌላው ግንባር መሳተፍ እንዳለበት አስረድተዋል።

አስር አለቃ መሸሻ እንዳሉት ኢትዮጵያውያን የመተባበር ነባር ባህላቸውን አጠናክረው መከላከያ ሠራዊቱን በስንቅና በሞራል በመደገፍ አገር ለማሻገር እየተረባረቡ ይገኛሉ።

"አሸባሪው ህወሓት በአካባቢያችን የጥፋት ወጥመዱን እንዳይዘረጋ የሰርጎ ገቦችንና ቅጥረኞችን እንቅስቃሴ  ከህዝቡ ጋር ሆነን እየጠበቅን ነው" ብለዋል።

"አዲስ ታሪክ የሚያስመዘግብ  ትውልድ አካል በመሆናችን እንኮራለን" ያሉት አሥር አለቃው፣ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ግንባር ለመሰለፍ ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።  

አገር ሰላም አስኪሆን ድረስ የተሰለፉባቸውን የአካባቢ ጥበቃ እና የስንቅ ዝግጀት ሥራዎች እንደሚያጠናክሩ አስር አለቃ መሸሻ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም