በአፍሪካ የውስጥ ፍልሰትን በተቀናጀ መንገድ ለመምራት የሚያስችል የሶሰት ዓመታት መርሃ ግብር ሊተገበር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የውስጥ ፍልሰትን በተቀናጀ መንገድ ለመምራት የሚያስችል የሶሰት ዓመታት መርሃ ግብር ሊተገበር ነው
አዲስ አበባ ነሃሴ 18/2010 በአፍሪካ አህጉር የሚካሄደውን የውስጥ ፍልሰት በተቀናጀ መልኩ ለመምራትና አህጉራዊ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል የሦስት ዓመታት መርሃ-ግብር በ35 አገሮች ሊተገበር ነው። መርሃ-ግብሩን በጋራ የሚያስፈጽሙት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ የዓለም ሥራ ድርጅትና የዓለም የፍልሰት ድርጅት ተወካዮች የጋራ መግባቢያ ሰነድ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተፈራርመዋል። መርሃ-ግብሩ ከስዊድን መንግስት በተገኘ የዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በሶስት ክፍለ-አህጉራዊ ማህበረሰቦች በሚገኙ 35 አገራት ይተገበራል ተብሏል። 'የተቀናጀ የሥራ ፍልሰተኞች አስተዳደር ለአፍሪካ ልማትና ትስስር' የተሰኘው መርሃ ግብሩ ለአፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ጥሩ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪ የአገራቱን ሰራተኛና ማህበራዊ ተቋማት አቅም ለመገንባት፣ የጋራ ፖሊሲና ስትራቴጂ ስርዓትን ለመንደፍ፣ የፍልሰተኞች ማህበራዊ ጥበቃና የተቃና ዝውውር እንዲፈጠር የጎላ ሚና ይኖረዋልም ተብሏል። በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ የኢጋድና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጉዳይ አስፈጻሚ ሚስ ሞሬን ኤቸንግ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ 82 በመቶ የሚገመተው የአፍሪካዊያን ዝውውር በአህጉሪቷ የሚደረግ ውስጣዊ ፍልሰት ነው። አፍሪካን በንግድ፣ በሰዎች ዝውውርና በአየር መንገድ ለማስተሳሰር ስምምነትና ሙከራ እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት፤ መርሃ-ግብሩ ተግባራዊ መደረጉ ጥሩ ታሪካዊ አጋጣሚ እንደሆነ አንስተዋል። "ፍልሰት በአግባቡ ከተመራ የላቀ ፋይዳ አለው" ያሉት ሚስ ሞሬን፤ በስነ-ሕዝብና ስራ አጥነት ገፊ ምክንያቶች የሚደረግ ውስጠ ፍልሰትን በተቀናጀ አግባብ መምራትና አህጉራዊ ትስስር መፍጠር እንደሚገባ ነው የገለጹት። የዓለም ሥራ ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ሴንታ ሳሙኤል በበኩላቸው፤ በአፍሪካ የሚደረግ የሥራ ፍልሰት አካታች በሆኑ ፕሮግራሞች ከተመራ ፍልሰት አዎንታዊ ጥቅሞች እንዲኖሩት፤ በአገራት መካከልም ትስስር እንዲፈጠር ያስችላል። በምስራቅ፣ ምዕራብና ደቡብ አፍሪካ የምጣኔ ሀብት ክፍለ አህጉራዊ ማህበረሰቦች ተግባራዊ የሚሆነው መርሃ ግብሩ፤ በአፍሪካ ውስጥ ለስራ ለሚዘዋወሩ ዜጎችና ቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆን የአህጉሪቷን የወደፊት ሁኔታ እንደሚለውጥ ተስፋ ተጥሎበታል። ሚስ ሴንታ እንደሚሉት 60 በመቶው የአፍሪካ ሕዝብ ከ25 ዓመት በታች የዕድሜ ክልል የሚገኝ ሲሆን የወደፊት የአፍሪካ ሕዝብ ቁጥር በአውሮፓ አቆጣጠር በ2030 ወደ 12 በመቶ፤ በ2050 ደግሞ 25 በመቶውን የዓለም ሕዝብ ቁጥር እንደሚሸፍን ይገመታል። ስለሆነም የወደፊት የዓለም ሰፊ ሕዝብ ቁጥር ባለቤት ለምትሆነው አፍሪካ የስራ ፍልሰቱንና ትስስርሩን ከወዲሁ በአግባቡ መምራት የሚያስችሉ አሰራሮችን መቀየስ ያስፈልጋል ብለዋል።