ባንኩ ወደ አገር ቤት ለሚገቡ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች ቀልጣፋ የምንዛሬ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል

45

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት ለሚመጡ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ቀልጣፋ የምንዛሬ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን ገለጸ።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ለኢዜአ እንደገለጹት ወደ አገር ቤት የሚገቡ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ለማስተናገድ ባንኩ የተለያዩ ዝግጅቶችን አድርጓል።

የተለያዩ ሕጋዊ የምንዛሬ አማራጮች፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የክፍያ መፈጸም ሥርዓትና የተቀላጠፈ የብድር አገልግሎት ለመስጠትም ተዘጋጅቷል።

ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ቡድኖችን ተዋቅረው ወደ ሥራ መገባቱን ነው ያስታወቁት።

ወደ አገር ቤት የሚመጡት ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች አገሪቷ ካለችበት ሁኔታ አንጻር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ከፍተኛ ዕድል የሚፈጥርላት መሆኑን ጠቁመዋል።

ከኢትዮጵያ ውጭ ገንዘብ የሚልኩ እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዳያስፖራዎች ሕጋዊ አማራጮችን ብቻ መጠቀም እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

ይህን በማድረግ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚዘዋወረውን የውጭ ምንዛሬ ወደ ሕጋዊ ሥርዓት እንዲመጣ ለአገራቸው አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉም ነው የባንኩ ፕሬዚዳንት የተናገሩት።

በጠላትነት ተሰልፈው ኢትዮጵያን መጉዳት የሚፈልጉ አገራት አንዱ የተሰለፉበት የውጭ ምንዛሬ እንዳታገኝ ማድረግ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የዚህ ዓላማ ተባባሪ ላለመሆን ሕጋዊ የምንዛሬ አገልግሎቶችን መጠቀም ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የባንኩ ኤ.ቲ.ኤም፣ ፖስ ሞባይል፣ ኢንተርኔትና ሁሉም ቅርንጫፎች ዳያስፖራውን ተቀብለው ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

በአዲስ አበባ 500፣ በመላ አገሪቷ 1 ሺህ 700፣ በኤርፖርት ውስጥ በሚገኙ ሁለት ቅርንጫፎችና ኤ.ቲ.ኤም ማሽኖች ቀልጣፋና ሕጋዊ  አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

የውጭ አገር ካርዶችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ ኤ.ቲ.ኤም ማሽኖችንም በመጠቀም በሕጋዊ መንገድ ምንዛሬ በማግኘት ለአገራቸው አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል የዳያስፖራ አባላት ለመኖሪያ ቤት፣ ለተሽከርካሪ እና ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ብድር የሚያገኙባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን አብራርተዋል።

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን አገራቸው ችግር ውስጥ በገባችበት ወቅት በሃሳብና በገንዘብ እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦ ለመልሶ ግንባታ በሚደረገው ርብርብም እንዲደግሙት ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም