በአሸባሪው ሕወሓት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር ፍላጎት ላላቸው ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች መንግስት አስፈላጊውን ትብብር ያደርጋል

55

አዲስ አበባ፤  ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የፈጸማቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርምሮ ለማጋለጥ ፍላጎት ላላቸው ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች መንግስት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ገለጸ።

መንግስት በአሸባሪ ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ፍትህ እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መግለጫ ሰጥቷል።

ሚኒስትር ደኤታዋ ሰላማዊት ካሳ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን መፈጸሙን አስታውሰዋል።

እንደ ሚኒስትር ደኤታዋ ገለጻ፤ የሽብር ቡድኑ በርካታ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጽም የዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ዳተኝነት አሳይተዋል።

'ሂውማን ራይትስ ዎች' ትናንት ታስቦ በዋለው የዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀን አሸባሪው የህወሃት ቡድን በጭና እና ቆቦ የፈጸመውን ወንጀል ይፋ ማድረጉ በጎ ጅምር መሆኑንም ተናግረዋል።

ሌሎች ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አሸባሪ ቡድኑ የፈጸመውን ወንጀል እንዲያጋልጡ ጥሪ አቅርበው፤ በዚህ ረገድ መንግስት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ስራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል እስካሁን ባለው ሂደት የተሟላ የወንጀል ምርመራ ማድረግ እንዲቻልና ወንጀለኞች ተጠያቂ በሚሆኑበት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪ ግብረ ኃይሉ ስደተኞችና በአሸባሪ ቡድኑ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች መልሰው በሚቋቋሙበት መንገድ ላይ ስራዎችን እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ግብረ ኃይሉ የራሱ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ተቋቁሞለት የሚያከናውናቸውን ተግባራት በተከታታይ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።

በሌላ በኩል የትምህርት ማሕበረሰብ የአንድ ሳምንት በጎ ተግባር አገልግሎት በተሳካ መልኩ መጠናቀቁን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።

በሳምንቱ ተማሪዎች የአርሶ አደሮችን ሰብል በመሰብሰብ፣ ደም በመለገስ፣ ስንቅ በማዘጋጀት እና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ደጋፍ በማሰባሰብ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ተማሪዎቹ በዚህ ተግባራቸው አገርና ህዝብ የመውደድ እሴትን በተግባር ያረጋገጡ በመሆኑ መንግስት ምስጋና ያቀርባል ብለዋል።

ይኸው ተግባር ቀጣይነት እንደሚኖረው አስታውሰው፣ ተማሪዎች ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ወደ ትምህርት ገበታቸው ይመለሳሉ ብለዋል።

መንግስት ከአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ሙሉ በሙሉ ነጻ የወጡ አካባቢዎች ከጸጥታ ስጋት ነጻ የማድረግ ስራ በስፋት እያከናወነ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም