ኢትዮጵያን ካለችበት ወቅታዊ ችግር ለማሻገር በስራ ሰዓት ሳንወሰን መስራት ይጠበቅብናል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ካለችበት ወቅታዊ ችግር ለማሻገር በስራ ሰዓት ሳንወሰን መስራት ይጠበቅብናል

ታህሳስ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ካለችበት ወቅታዊ ችግር ለማሻገር ሁላችንም በስራ ሰዓት ሳንወሰን ተጨማሪ ጊዜ ሰጥተን መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት ሰራተኞችና አመራሮች ገለፁ።
በፓርቲው የሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ መስከረም አበበ፤ ካለንበት የኢኮኖሚ ጫና በፍጥነት ለመውጣት በየመስኩ መረባረብ አለብን ብለዋል።
ግንባር ዘምተው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እያስጠበቁ እንዳሉ ጀግኖች ሁሉ ሁላችንም በተሰማራንበት ሙያ ውጤታማ በመሆን ለአገራችን መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ወቅታዊ ችግር ለማሻገር በስራ ሰዓት መወሰን እንደማያስፈልግም ገልጸዋል።
የፓርቲው የፋይናንስ አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ አቶ ዘነበ ኩሞ፤ ኢትዮጵያ በአውደ ውጊያ ያሳካችውን ድል በኢኮኖሚው ግንባር ለመድገም መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የውጭ ሃይሎች በእርዳታ ስም የሚያደርጉትን ጫና ለመቋቋም በተለይም በግብርናው ዘርፍ ጠንክሮ በመስራት ጫናውን ልንቋቋም ይገባል ነው ያሉት።
በፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያው አቶ ታምራት ማለደ በበኩላቸው ኢኮኖሚው እንዲያገግም ለማድረግ በተለይ የመንግስት ሰራተኛው መደበኛ የስራ ሰዓት ሊገድበው እንደማይገባ አስገንዝበዋል።
የሰንዳፋ በርክ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሺኔ ዳዲ፤ በአውደ ውጊያ የተገኘውን ድል በኢኮኖሚው ግንባር ለመድገም ጠንክረን መስራት አለብን ብለዋል።
የፓርቲው ፅህፈት ቤት ሰራተኞችና አመራሮች በሰንዳፋ በርክ ወረዳ ዳቤ ሙዳ ጎዶ ቀበሌ ተገኝተው የዘማች ቤተሰቦችን የደረሰ የስንዴ ሰብል ሰብስበዋል።
_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።