የደቡብ እና የኦሮሚያ ክልሎች ለአገር መከላከያ ሰራዊት የአይነት ድጋፍ አደረጉ

42

ታህሳስ 1/2014/ኢዜአ /የደቡብ እና የኦሮሚያ ክልሎች ለአገር መከላከያ ሰራዊት 64 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ አደረጉ።

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እና የኦሮሚያ ክልል ለአገር መከላከያ ሰራዊት ያዘጋጁትን ስንቅ በዛሬው እለት አስረክበዋል፡፡

የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ፤ ከዚህ ቀደም ክልሉ ለሰራዊቱ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በዛሬው እለት ደግሞ ለአምስተኛ ጊዜ 52 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የሚገመት የስንቅ ድጋፍ መደረጉን ገልጸው ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኦሮሚያ ክልል የድጋፍ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ፈይሳ፤ ለአገር ሉአላዊነት እየተፋለመ ለሚገኘው ሰራዊት 12 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ሰንጋዎችን ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ህዝብና መንግስት እስካሁን ለመከላከያ ሰራዊት 90 ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

የሁለቱን ክልሎች ድጋፍ የተቀበሉት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ  ሉዊጂ፤ ክልሎቹ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም