የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበራት ኅብረት አባላት ለመከላከያ ሠራዊት ደም ለገሱ

44

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 01/2014 (ኢዜአ) የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበራት ኅብረት አባላት ለመከላከያ ሠራዊት ደም ለግሰዋል።

ኅብረቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች አንድ ሚሊዮን ብር እንዲሁም ከሠራተኞችና ከአመራር አባላት ደመወዝ 497 ሺህ ብር ተቀንሶ ገቢ እንዲሆን መወሰኑም ተገልጿል።

የኅብረቱ አባል ድርጅቶች 120 ሠራተኞች ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን መቆማቸውን ለመግለጽ ዛሬ ደም ለግሰዋል።  

ከደም ለጋሾቹ መካከል ወይዘሮ ታሪክ አስቻለው ደም ለመለገስ ያስቡ እንደነበረ ገልጸው አሁን ባገኙት አጋጣሚ ለመከላከያ ሠራዊት መለገሳቸውን ገልጸዋል።

አቶ ግርማ አመንቴ በበኩላቸው በግንባር እየተዋደቀ ለሚገኘው ሠራዊት ደም መለገስ በግንባር እንደ መገኘት ይቆጠራል ነው ያሉት።

ወይዘሮ ሳራ ወርቁ ደግሞ ግንባር መሄድ ባልችልም ስንቅ በማቀበል፣ ደም በመለገስ እና የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ በፈቃደኝነት ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ የምትገኝ መሆኗን በመረዳት "ሁላችንም በምንችለው አቅም ማገዝ ይኖርብናል" ነው ያሉት።

የኅብረቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ንጉሱ ለገሰ በጦርነቱ ሳቢያ በአፋርና በደብረ ብርሃን ለሚገኙ ተፈናቃዮች አንድ ሚሊዮን ብር እንዲሁም ከሠራተኛውና ከአመራሩ ደመወዝ 497 ሺህ ብር ተቀንሶ ገቢ እንዲሆን መወሰኑን ገልጸዋል።

ዶክተር ንጉሱ አያይዘውም የዳያስፖራው ማኅበረሰብ እያደረገ ላለው የአንድነት ትግል በኅብረቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም