አንዳንድ ምዕራባውያን የሚያሳድሩት ጫና የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አንዳንድ ምዕራባውያን የሚያሳድሩት ጫና የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው
ባህርዳር ታህሳስ 1/2014 (ኢዜአ) አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት አሸባሪው ህውሃትን በመደገፍ በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩት ጫና የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ነው ሲሉ የህግ ምሁራን ገለጹ።
በአማራ ክልል የፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ኢንስቲትዩት የስልጠና ዳይሬክተር አቶ አበበ ካሴ እንደገለጹት አሸባሪው ህውሃት የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊትን በማጥቃት አሸባሪነቱን በድርጊቱ አረጋግጧል።
በአማራና አፋር ክልሎች ላይ ወረራ በመፈጸም በደረሰባቸው አካባቢዎች ንጹሃንን በጅምላ በመጨፍጨፍ፣ በቡድን በመድፈር፣ ሃብትና ንብረት በመዝረፍና በማውደም በአሸባሪነቱ መቀጠሉን ጠቅሰዋል።
አለም አቀፍ ገጽታ ያለውን ሽብርተኝነትን የማጥፋት መርህን ወደ ጎን በመተው በህዝብ የተመረጠ መንግስት ላይ ጫና ሲፈጥሩ ማየት አገር ለማፍረስ ካላቸው ፍላጎት የመነጨ መሆኑንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የጸረ ሽብር ህግ በማውጣት አሸባሪዎችን እየተፋለመችና ሽብርተኝነትን እየተከላከለች ብትሆንም ከተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት እየደረሰባት ያለው ጫና ከመርህ ውጭ መሆኑን ተናግረዋል።
አንዳንድ የምዕራባውያን ሃያላን አገራት ፍላጎታቸውን በሌላው ላይ በማስረጽ ለነሱ የሚታዘዝ መንግስት በመፍጠር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ፍላጎታቸውን ማስፈጸም ከጥንት ጀምሮ የሚተገብሩት ድርጊታቸው ነው።
"ዓላማና ግባቸውን ለማሳካት ከአለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ጫና ባሻገር አሁን በኛ አገር ላይ እንዳደረጉት ጠንካራ አገርና መንግስትን የሚያዳክሙ ቡድኖችን ሲደግፉ ማስተዋል የተለመደ ተግባራቸው ነው" ብለዋል።
አለም በመርህና በህግ መመራት አለባት ቢባልም በተግባር የሚታየው በኢኮኖሚና በፖለቲካ አቅም ያላቸው አንዳንድ ምዕራባውያን መንግስታት ታዳጊ አገራትን ለመቆጣጠር ሽኩቻ ውስጥ ሲገቡ መሆኑን አስረድተዋል።
በውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አንዳንድ ምእራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ጫና ለመፍጠር እያደረጉ ያለውን ዘመቻ በመቃወም እያሳዩ ያለውን ትግል አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በኢንስቲትዩቱ የህግ ተመራማሪ አቶ ይማም ሰይድ በበኩላቸው የተባበሩት መንግስታት ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል የሚያስችሉ ህጎችን በማውጣት ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ያወጣቸውን ህጎች በመተግበር በኩልም የፈረሙና ያልፈረሙ አገራት ሽብርተኝነትን መደገፍ እንደሌለባቸውና በጋራ ለመከላከል ተስማምተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ነገር ግን አንዳንድ የውጭ መንግስታት በኢትዮጵያ ህዝብ ይሁንታ አግኝቶ ከተመረጠው መንግስት ይልቅ የህወሃት ሽብርተኛ ቡድንን መደገፋቸው ከአለም አቀፍ መርህ ውጭ መሆኑን አብራርተዋል።
"የአንዳንድ ምዕራባውያን መንግስታት በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩት ሴራና ጫና ተጠናክሮ መቀጠሉ ህግን መሰረት ያደረገ ሳይሆን ግላዊ ጥቅማቸውን ለማሳካትና አፍሪካን በእጅ አዙር ለመጠምዘዝ ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ነው" ብለዋል።
የውጭ ታሪካዊ ጠላትንና የውስጥ ተላላኪን ለመፋለም መላ ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በቁርጠኝነት በመሰለፍ የአድዋን ድል ዳግም በመድገም ታሪካችንን ማደስ አለብን ሲሉ" ምሁራኑ አስገንዝበዋል።