በአሜሪካ ሜሪላንድ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ሊካሄድ ነው

65

ታህሳስ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ)  በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ታህሳስ 17 ቀን 2014 ዓ.ም በአሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት እንደሚካሄድ ተገለጸ።

ዝግጅቱ "የዚህ ዓመት የገና ስጦታዬ ለተፈናቀለው ኢትዮጵያዊ ወገኔ"  በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ አስተባባሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በሜሪላንድ ግዛት በምትገኘው 'ሲልቨር ስፕሪንግ' ከተማ በሚካሄደው ዝግጅት ታዋቂ የባሕላዊና ዘመናዊ ሙዚቀኞች የሚሳተፉበት ዝግጅት እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል።

በዝግጅቱ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ የንግድ ማኅበረሰብና ተቋማት፣ የሃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚታደሙ ተጠቁሟል።

ከዝግጅቱ የሚሰበሰበው ገንዘብ ለገና በዓል ስጦታ በሚል በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እንደሚደረግም ነው የተነገረው።

የገቢ ማሰባሰቢያው በውጭ የሚኖረው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ከወገኑ ጎን መቆሙን እንዲሁም ያለውን ኢትዮጵያዊ አንድነትና ሕብረት የሚያሳይበት እንደሆነም የመርሃ ግብሩ አስተባባሪዎች ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩን ያዘጋጁት ሚስ ኢትዮጵያ ዩኤስኤ ፓጀንት ከኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ከአርቲስቶች እና ከማህበረሰብ ከንግድና ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በመተባበር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም