በምዕራብ ጎንደር 7 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ የመስኖ ልማት ተጀመረ

56

መተማ፣ ታህሳስ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን በበጋ መስኖ 7 ሺህ 500 ሄክታር መሬት የማልማት ሥራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የመስኖ ልማት ባለሙያ ወይዘሮ ረፍረፍ ሙሃመድ ለኢዜአ እንዳሉት የህወሓት የሽብር ቡድን በከፈተው ጦርነት ምክንያት በመኽር ከለማው ሰብል ሊታጣ የሚችለውን የሰብል ምርት በመስኖ ለማካካስ እየተሰራ ነው።

አማራጭ ውሃ ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ አቅምን አሟጦ በመስኖ ለማልማት ብርቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ከሚለማው መሬት ውስጥ 5 ሺህ ሄክታሩ በቆላ ስንዴ የሚለማና ቀሪው መሬት በጓሮ አትክልትና በሌሎች ሰብሎች ዘር የሚሸፈን መሆኑን ተናግረዋል።

ባለሙያዋ እንዳሉት እስካሁን ባለው የበጋው ጊዜ 942 ሄክታር መሬት ታርሶ በተለያዩ ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል።

ቀሪውን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን የእርሻ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ነው የገለጹት።

በመጀመሪያው ዙር  በስንዴና በተለያዩ የጓሮ አትክልቶች ከሚለማው መሬት 566 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ "በልማቱ ከ18 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ይገኛል" ብለዋል።

በተያዘው የበጋ ወቅት የሚለማው መሬት ካለፈው አመት በ6 ሺህ ሄክታር ብልጫ ያለው መሆኑን ገልጸው፣ የሚገኘው ምርት ባለፈው ዓመት ከተገኘው በ299 ሺህ ኩንታል ብልጫ እንደሚኖረው አመላክተዋል ።

ወይዘሮ ረፍረፍ እንዳሉት በመስኖ ልማቱ እየተሳተፉ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የምርት ማሳደጊያ ግብዓት ከማቅረብ ባለፈ የባለሙያ እገዛ እየተደረገ ይገኛል።

መስኖ ልማቱን ለማሳለጥም ከ60 በላይ ባለ 50 የፈረስ ጉልበት የውሃ መሳቢያ ጄነሬተሮች ለአርሶ አደሮች መከፋፈሉንም አስታውቀዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት በተካሄደ የመስኖ ልማት 267 ሺህ ኩንታል ምርት መሰብሰብ እንደተቻለ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም