ኢትዮጵያዊያን በሁሉም ግንባር የተከፈተብንን ጦርነት በጋራ መቀልበስ አለብን

72

ታህሳስ 1/2014/ኢዜአ/ ኢትዮጵያዊያን በሁሉም ግምባር የተከፈተብንን ጦርነት በጋራ መቀልበስ አለብን ሲሉ የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።

ሚኒስትሯ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ የውጭ አገር የስራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲዎች አሰሪ ፌዴሬሽን ለአገር መከላከያ ሠራዊት የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍና ደም ልገሳ ባደረገበት ወቅት ነው።

የፌዴሬሽኑ አባላት በተጨማሪም በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምትያላቸው የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አሰባስበዋል።

በደም ልገሳው የተሳተፉት ሚኒስትር ሙፈሪያት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአፋርና በአማራ ክልሎች በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የበኩሉን ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን በዜጎች እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አንስተው 'የገጠሙንን ፈተናዎች ለማለፍ በጋራ መስራት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።

ሁላችንም በየተሰማራንበት መስክ ጠንክረን በመስራት አገራችንን ካለችበት ወቅታዊ ችግር ማላቀቅ ይጠበቅብናል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

ጊዜው እጃችንን ጠምዝዘው ፍላጎታቸውን ሊጭኑብን ለሚሹ የውጭ ኃይሎች አንድነታችንን የምናሳይበት ነው ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ አገር የስራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲዎች አሰሪ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ነቢል መሐመድ በበኩላቸው ለአገር መከላከያ ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ፌዴሬሽኑ የበኩሉን እንደሚወጣም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም