በመናሲቡ ወረዳ በርካታ ተተኳሽ ጥይቶች የተገኘበት ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

64

ጊምቢ ፤ ታህሳስ 1/2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን መናሲቡ ወረዳ ተተኳሽ ጥይቶችን በተሽከርካሪ ጭኖ ሲያጓጉዝ የተገኘ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ አስታወቀ።

የኮሚቴው አባል ሳጅን ፉዓድ አወል ሑሴን እንደገለጹት፤ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር የዋለው ህብረተሰቡ ባደረገው ጥቆማ የወረዳው የፀጥታ አካላት ባደረጉት የተቀናጀ ክትትል ነው፡፡

ተጠርጣሪው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 - 74409 ኢት በሆነ የጭነት ተሽከርካሪ ከላይ መጠጥ ከስር የክላሽንኮቭ ተተኳሽ ጥይቶችን ደብቆ ጭኖ  ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ በመጓዝ ላይ እንዳለ እንደተደረሰበት አስረድተዋል።

በወረዳው ልዩ ስሙ ጎምቦ ቂልጡ ጃሌ  በተባለ አካባቢ  በቁጥጥር ስር በማዋል ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር አያደረገ ያለውን ትብብር  አጠናክሮ እንዲቀጥልም ሳጅን ፉዓድ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኅብረተሰቡም ከምንጊዜውም በላይ ተደራጅቶ ከአሸበሪዎቹ ህወሀትና ሸኔ ሰርጎ ገብ የጥፋት ተላላኪዎች አካባቢውን በንቃት መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም