የጅማ አባጅፋሩ ኦኪኪ አፎላቢ ለስድስት ወራት ከእግር ኳስ ተሳትፎ ታገደ - ኢዜአ አማርኛ
የጅማ አባጅፋሩ ኦኪኪ አፎላቢ ለስድስት ወራት ከእግር ኳስ ተሳትፎ ታገደ
አዲስ አበባ ነሀሴ 18/2010 በተጭበረበረ ፊርማ ለግብጹ ክለብ ኢስማዒሊያ ውል ፈርሟል የተባለው ናይጄሪያዊው የጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ ለስድስት ወራት ከየትኛውም የእግር ኳስ ተሳትፎ እንዲታገድ ተወሰነ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው ተጫዋቹ ለፈጸመው ጥፋት በተጨማሪም 25 ሺህ ብር ቅጣት እንዲከፍል ውሳኔ ተላልፎበታል። 23 ግቦችን በማስቆጠር የዘንድሮው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የጨረሰው ኦኪኪ አፎላቢ እገዳው የተላለፈበት በተጭበረበረ ፊርማ ለግብጹ ክለብ ኢስማዒሊያ ውል መፈረሙን ተከትሎ ነው። ተጫዋቹ ሐምሌ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተጫዋቾችን ዝውውርና አጠቃላይ መረጃ በሚቆጣጠርበት የመረጃ ቋት በፊርማ ማጭበርበር መያዙ ታውቋል። ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የስነ-ምግባር ኮሚቴ ኦኪኪ አፎላቢን ለስድስት ወራት ከየትኛውም የእግር ኳስ ተሳትፎ እንዲታገድ ወስኗል። በዚህም መሰረት ውሳኔውን ለዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ያሳወቀ ሲሆን የፊፋ ውሳኔ የሚጠበቅ ይሆናል።