አሸባሪው ህወሓት ያደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት የማጥናት ሥራ ነገ ይጀመራል

ባህር ዳር፤ ህዳር 30 ቀን 2014 (ኢዜአ ) አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ያደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት የማጥናት ሥራ ነገ እንደሚጀመር የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በጥናቱ ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር የውይይት መድረክ በባህር ዳር ተካሄዷል።

የቢሮ ሀላፊ አቶ አንሙት በለጠ እንደገለፁት አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ያደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት የማጥናት ስራ ነገ ይጀመራል።
በክልሉ ከሚገኙ 10 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን፣ የ11 የክልል ተቋማት ባለሙያዎችና ወረራ የተፈፀመባቸው ሰባት ዞኖች ተወካዮች በጥናቱ እንደሚሳተፉም ገልፀዋል።
የጥናቱን ግኝት መሰረት በማድረግ መንግስት በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ የሚያቋቁማቸውን እና የሚገነባቸውን መሰረተ ልማቶችን የመለየት ስራ እንደሚያከናውን ገልጸዋል።

የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ከባለሀብቶች፣ ከልማት ድርጅቶች፣ ከዳያስፖራውና ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሀበት የማሰባሰብ ሥራ እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ማደረሱን ጠቁመዋል።
ከአሸባሪው ህወሓት ነፃ በወጡ አካባቢዎች የህዝብ መገልገያ ተቋማትን አገልግሎት ለማስጀመርና መልሶ ለማቋቋም ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

የጥናቱ ግኝት የክልሉን መብትና ጥቅም ከማስከበር ባለፈም አሸባሪው ህወሓት በአጠፋው መጠን ፍርድ እንዲያገኝ እንደሚያግዝም አመልክተዋል።

ነፃ በወጡ አካባቢዎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመርም ሆነ በዘላቂ መንግድ ችግሩን ለመፍታት ለሚካሄደው ጥናት ህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ሰብሳቢ ዶክተር  ታፈረ መላኩ እንዳሉት የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ፈፅሟል፤ የመሰረተ ልማት አውታሮችን አውድሟል።
በአሸባሪው ህወሓት የተፈፀመው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፈውበት የሚካሄደው ጥናት ግኝት ለህዝብና ለመንግሥት ይቀርባልም ብለዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ የእቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ተክለ ሃይማኖት ገብረ ህይወት በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት ሆስፒታሎችን ጨምሮ በጤና ጣያዎች፣ጤና ኬላዎችና በደም ባንክ ማዕከላት ላይ ዘረፋና ውድመት ፈፅሟል።
በደረሰውን ውድመትና ዝርፊያ ዙሪያ ሳይንሳዊ ጥናት መደረጉ በጤና ተቋማት መዘረፍ ምክንያት በእናቶችና ህፃናት ተገቢውን ህክምና ባለማግኘታቸው የሚከሰትን ወረርሽኝ በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት ያግዛል።

በውይይት መድረኩ የዩኒቨርስቲ ምሁራንን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም