የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለመስጠት ተዘጋጅቷል

150

አዲስ አበባ ህዳር 30/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተያዘው በጀት ዓመት ለግሉ ዘርፍ፣ ለግብርና ግብዓትና ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለመስጠት መዘጋጀቱን ገለጸ።

መንግስት አስቀምጦት የነበረው የብድር ክልከላ መነሳት የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ተነግሯል።

የኢኮኖሚ አሻጥሮችና የጥቁር ገበያውን መቆጣጠር እንዲቻል የግል እና የመንግስት ባንኮች የሚሰጡትን ብድር በጊዜያዊነት እንዲያቆሙ ተደርጎ እንደነበረ ይታወቃል።

ይሁንና ለሶስት ወራት ተጥሎ የቆየው ክልከላ መነሳቱ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ነው የተገለፀው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድርና ሃብት አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉነህ ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት ባንኩ በዚህ ዓመት ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለመስጠት ተዘጋጅቷል።

ከዚሁ ገንዘብ ውስጥ 25 ቢሊዮን ብር ለግሉ ዘርፍ፣ 30 ቢሊዮን ብር ለግብርና ግብዓት ሲሆን ቀሪው ለመንግስት የልማት ድርጅቶች እንደሚውል አብራርተዋል።

ገንዘቡ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ሁኔታ ያነቃቃል፤ ለስራ ፈጠራም አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

በባንኮች ላይ የተጣለው የብድር ክልከላ የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት ጊዜያዊ መፍትሔ በመሆኑ ትክክለኛ እርምጃ ነው ያሉት አቶ ሙሉነህ ክልከላው ሕገወጦችን መቆጣጠር እንዳስቻለ ተናግረዋል።

ነገር ግን በባለሃብቶች የሚካሔደውን ኢንቨስትመንት ማሳደግና ስራ መፍጠር እንዲቻል የባንኮች የብድር አገልግሎት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

ባንኮች ከዋነኛ ተግባራቸው አንዱ ብድር መስጠት መሆኑንና ከሚሰጡት ብድር የሚያገኙት ትርፍም ተመልሶ ጥቅም ላይ እንደሚውል አክለዋል።

እንደ አቶ ሙሉነህ ገለጻ የብድር ክልከላው መነሳት ተቋርጠው የነበሩ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው የስራ ዕድል እንዲከፍቱ ማድረግም ያስችላል።

በዚሁ መሰረት በተለይ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልጋቸው የብድር ገንዘብ ተለቆላቸው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም