ኢትዮጵያ በፊፋ የአገሮች እግር ኳስ ደረጃ አንድ ደረጃ ዝቅ ብላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በፊፋ የአገሮች እግር ኳስ ደረጃ አንድ ደረጃ ዝቅ ብላለች
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ዛሬ ባወጣው የግንቦት ወር የአገሮች የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ አንድ ደረጃ ዝቅ ብላለች። በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ በሚያዚያ ወር ከነበረችበት 145ኛ ደረጃ ወደ 146ኛ ዝቅ አለች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም በኬንያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች የዋንጫ ውድድር በኋላ ምንም አይነት ጨዋታዎችን አድርጎ አያውቅም። የቡድኑ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ታህሳስ ወር ላይ ስራቸውን ከለቀቁ በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እስካሁን አዲስ አሰልጣኝ አልሾመም። የኢትዮጰያ ብሔራዊ ቡድን በ2019 በካሜሮን ለሚካሄደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለማለፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን በመጪው ነሐሴ ከሴራሊዮን አቻው ጋር የሚጫወት ይሆናል። በፊፋ የአገሮች የእግር ኳስ ደረጃ ጀርመን፣ ብራዚል፣ ቤልጂየም፣ ፖርቹጋልና አርጀንቲና ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ የያዙ ሲሆን ስዊዘርላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ቺሊና ፖላንድ ከስድስት እስከ አስር ባለው ደረጃ ተቀምጠዋል። ሴኔጋል 28ኛ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 38ኛ፣ ሞሮኮ 42ኛ፣ ግብጽ 46ኛ እና ናይጄሪያ 47ኛ ደረጃ በመያዝ ከአፍሪካ የተሻሉ ሆነዋል። ዛሬ በወጣው ደረጃ ከ1 እስከ 47ኛ ባለው ደረጃ የተቀመጡት አገሮች ከባለፈው ወር ምንም የደረጃ ለውጥ አላሳዩም። ኩዌት 16 ደረጃዎችን አሻሽላ ወደ 160ኛ በመምጣት በወሩ ከፍተኛ የደረጃ መሻሻል ያሳየች ሲሆን በአንጻሩ ፍልስጤም 13 ደረጃ በመቀነስ ወደ 96 ወርዳ በወሩ በከፍተኛ ደረጃ ያሽቆለቆለች አገር ሆናለች። አንጉሊያ፣ ባህማስ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ቶንጋ የመጨረሻውን 207ኛ ደረጃ ይዘዋል። በሴቶች የፊፋ የአገሮች የእግር ኳስ ደረጃ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎቹ 118ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የፊፋ ወርሐዊ የአገሮች ደረጃ የሚወጣው ፊፋ እውቅና በሰጣቸው ውድድሮች ላይ ብሔራዊ ቡድኖች ባስመዘገቡት ውጤት በሚሰጣቸው ነጥብ አማካኝነት ነው።