ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሠራተኞች በአፋር ክልል ለመከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቃዮች ድጋፍ አደረጉ

ህዳር 30/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሠራተኞች በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ከተማ በመገኘት ለመከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ አድርገዋል።
ሠራተኞቹ ለመከላከያ ሠራዊት ደም ለግሰዋል፤ የአንድ ወር ደመወዛቸውን እንዲሁም በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉ ዜጎችም ምግብ ነክ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ፤ አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦል ድረስ እሄዳለው ያለውን ለመቀልበስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።

ለቀጣዩ ትውልድ የታፈረችና የተከበረች ኢትዮጵያን ማሻገር እንደሚገባ፤ ለዚህም የሚከፈለው መስዋዕትነት መጠናከር እንደሚኖርበት አመልክተዋል።

ኢንስቲትዩቱ በአሸባሪው ቡድን ለችግር የተጋለጡ ሴቶች ሕጻናትና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለማገዝ  ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል።  

 የሕልውና ዘመቻው ከተጀመረ አንስቶ ለመከላከያ ሠራዊት ደም በመለገስና በገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መሄዳቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን በወራሪው ላይ እየተቀዳጁት ያለው ድል "ኢትዮጵያን ለመንካት ለሚያስብ ሁሉ ደጋግሞ ማሰብ እንዳለባቸው የሚያስተምር" የታሪክ ምዕራፍ ነው ብለዋል።

የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግርማ ደጀኔ በበኩላቸው ተቋሙ ከሕልውና ዘመቻው ጋር በተያያዘ ለሠራዊቱ የአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችን በሁሉም መስክ መልሶ ማቋቋም የሁላችንም የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ይሽሩን ዓለምአየሁ ናቸው።

የተቋሙ ሠራተኛ ዶክተር ሰብሉ ሁምኔ በበኩላቸው አንድነታችንን አጠናክረን ከመንግሥት ጎን በመቆም አሸናፊነታችንን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ተወካይ ብርጋዴል ጄኔራል ተመስገን አቦሴ ለኢትዮጵያ ሕዝብ "ደግመን ደጋግመን ብንሞት፣ ብንቆስል፣ ደማችንን ብናፈስ የሚቆጨን አይደለም" ብለዋል።

"የማይነጥፍ የሕዝባችን ድጋፍ ከጀርባችን ስላለ" ይሄን ጠላት እንደመስሰዋለን ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም