ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሠራዊት በደቡብ ሶማሊያ ክልል ለተገኘው አንጻራዊ ሠላም አስተዋጽኦው የጎላ ነው -የክልሉ ፕሬዝዳንት

ሶማሊያ ነሀሴ 18/2010 የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በደቡብ ሶማሊያ ክልል ለተገኘው አንጻራዊ ሠላም የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው የክልሉ ፕሬዝዳንት ሻሪፍ ሀሰን ሼክ አዳን ተናገሩ። የተገኘውን ሠላም አስተማማኝ ለማድረግ ከአሚሶምና ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩም ነው ያረጋገጡት። ፕሬዝዳንት ሻሪፍ ሀሰን ሼክ አዳን እንደተናገሩት ቀደም ሲል የደቡበ ሶማሊያ አካባቢ አልሸባብን ጨምሮ በተለያዩ የሽብር ቡድኖች ትታመስ ነበር። ይሁንና በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ሠራዊት (አሚሶም) ወደ ስፍራው ካቀና በኋላ በአካባቢው የነበረውን ሰላም ዳግም ለመመለሰ ተችሏል። በዚህም በአካባቢው የተጋጩ ጎሳዎችና ቡድኖች እንዲታረቁ መደረጉንና በአሁኑ ወቅት ነዋሪው በተሻለ መልኩ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ የአሚሶም ሠራዊትና የሕዝቡ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑንና የኢትዮጵያ ሠራዊትም ለረጅም ጊዜ አዎንታዊ ሚና መጫወቱን ተናግረው ለሠራዊቱ ምስጋና ቸረውታል። በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በእያንዳንዱ ወረዳዎች 300 ልዩ የፖሊስ ኃይል (ሚሊሻ) እንዲሰለጥንና እንዲታጠቅ አድርገናል ብለዋል። ልዩ የሚሊሻ ኃይሎቹን በሙያ የተካኑ ለማድረግም የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ሠራዊት (አሚሶም) በሥልጠና እገዛ ማድረጉንም ነው የገለጹት። ይህም ኃይል አሚሶም ከወጣ በኋላም በአካባቢው ዘላቂ ሠላም ለማምጣት ያለውን ሚና ከግምት በማስገባት በክልሉ መንግሥት ታምኖበታል ነው ያሉት። አሁን ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም ከነበረው አለመረጋጋት የተሻለ ሰላም ቢኖርም አሁንም አልሸባብ ኅብረተሰቡ ውስጥ ስጋት መሆኑ አልቀረም ብለዋል። በመሆኑም የተገኘውን ሠላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ከአሚሶም፣ ከመላ ሕዝቡና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በደቡብ ምዕራብ ሶማሌ ከሁለት ዓመታት በፊት የተመሰረተውን ምክር ቤት የሚመሩት አብድል ከሪም ሸሪፍም የፕሬዚዳንቱን ሃሳብ ይጋራሉ። እንደ ምክር ቤትም ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ሰላም የሚያመጡ ሥራዎችን መሥራታቸውን ጠቅሰው ይህንኑ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል። በተለይም የፕሬዝዳንት ምርጫውን በሕዝብ ውሳኔ መሰረት ለማድረግ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ክልል በአሚሶም ቀጣና ሦስት ሥር በኢትዮጵያ የሚተዳደር ሥፍራ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም