በአሚሶም ሥር የተሰማራው አራተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሠራዊት ግዳጄን በተሳካ ሁኔታ እየፈጸምኩ ነው አለ - ኢዜአ አማርኛ
በአሚሶም ሥር የተሰማራው አራተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሠራዊት ግዳጄን በተሳካ ሁኔታ እየፈጸምኩ ነው አለ
ሶማሊያ ነሀሴ 18/2010 በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሠላም አስከባሪ ሠራዊት (አሚሶም) ሥር የተሰማራው አራተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሠራዊት ግዳጁን በተሳካ ሁኔታ እየፈጸመ መሆኑን አስታወቀ። በአሚሶም ሥር ስድስት የአፍሪካ አገራት የተሳተፉበት የሠራዊት ቀጣናዎች በሶማሊያ ተመስርተዋል። ከእነዚህም “ቀጣና ሦስት” በኢትዮጵያ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ የሚተዳደር ሲሆን በሌሎች ሁለት ቦታዎች ደግሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት በከፊል ያስተዳድራል። ሠራዊቱ የሶማሊያ ሕዝብና መንግሥትን የመደገፍ ተልዕኮውን ሲሰራ መቆየቱን የቀጣና ሦስት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አሰፋ ቸኮል ይናገራሉ። ለሶማሊያ ፖሊስ፣ ሚሊሺያ፣ ለክልልና ለመደበኛ የሶማሊያ ጦር ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጥቶታል ብለዋል። ለሕዝቡ የጸጥታ ሥራ በመሥራት መተማመን በመፍጠርና ወገንተኝነቱን በማሳየት በቅርበት ሲሰራ መቆየቱን ነው የገለጹት። አጫጭርና ረጃጅም ጉዞዎችን በመጓዝም የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ የተለያዩ የዘመቻ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል። በዚህም በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን ጠቅሰው ይህም ሰራዊቱ ግዳጁን በአግባቡ መወጣቱን ያሳያል ብለዋል። ሠራዊቱ የአልሸባብን የውጊያ ስልት በቅጡ በማጤን የሽብር ቡድኑ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የሚያደርሰውን አደጋ መመከት ተችሏል ነው ያሉት። በዚህም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መሬት ላይ የተቀበሩ 56 ፈንጂዎችን ማምከን ተችሏል ብለዋል። ጎን ለጎንም ሠራዊቱ በልማት ሥራዎች ላይ በመሰማራት የሶማሊያ ሕዝብና መንግሥትን ለመደገፍ ሲሰራ መቆየቱንም አስረድተዋል። ከእነዚህም መካከል የውኃ መስመር ዝርጋታዎችና በአልሸባብ የተዘጉ መንገዶችን ለማስከፈት የመንገድ ጥርጊያ መሰራቱን ጠቅሰዋል። ከዚህ ባሻገር ሠራዊቱ ከመደበኛ ቀለቡ ተቀናሽ በማድረግ ለተፈናቃዮች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፎችን አድርጓል። ሰራዊቱ ለዚህ ስኬት የበቃው ከአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ከጎሳ መሪዎች፣ ከሴትና ከወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም ከአስተዳደርና የጸጥታ መዋቅር ጋር በጋራ በመስራት ነው ብለዋል። ከኅብረተሰቡ ተወካዮች ጋር በየሳምንቱ መደበኛ ሰብሰባ መኖሩን ጠቁመው አልፎ አልፎም በጋራ የጸጥታ ጉዳይ ላይ የሶማሌያ ጦር እኩል ተሳታፊ የሚሆንበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ በምታስተዳድረው የአሚሶም የጦር ቀጣና ከ350 በላይ የአልሸባብ አባላት ተማርከዋል፤ የሞቱም አሉ። በአሚሶም ሥር የተሰማራው አራተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሠራዊት የዓመት ግዳጁን ፈጽሞ ለተከታዩ ዙር ኃላፊነቱን እያስተላለፈ ነው። በኢትዮጵያ ሠራዊት ሥር የሚተዳደረው ሥፍራ ከአጠቃላዩ የአሚሶም የሶማሊያ ጦር ይዞታ ሽፋን 74 በመቶ ይሸፍናል። በዚህም ከአራት ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ጦር ሰፍሯል። ይህም በሶማሊያ ከተሰማራው ሠራዊት ከኡጋንዳ ቀጥሎ ኢትዮጵያን በሰራዊት ብዛት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል።