ዩኒቨርሲቲው የነቀምቴ ከተማን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ የሚያሳይ መጽሐፍ አዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የነቀምቴ ከተማን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ የሚያሳይ መጽሐፍ አዘጋጀ
ነቀምቴ ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን በሚሰጠው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የነቀምቴ ከተማን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ የሚያሳይ መጽሐፍ አዘጋጅቶ ለከተማ አስተዳደሩ አበረከተ ፡፡
የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት፣ ምርምርና ኢንዱስትሪ ትስስር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዲሪባ ዲባ መጽሐፍን ለከተማ አስተዳደሩ ትናንት አስረክበዋል።
ዶክተር ድሪባ በወቅቱ እንደገለጹት መጽሐፉ የከተማውን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ መሠረታዊ መረጃዎችን ይዟል።
"መጽሐፉ ለከተማው እድገት አስፈላጊውን ዕቅድ በማዘጋጀት በልማት ስራ ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለ ሀብቶችና ኢንቨስተሮች አስፈላጊውን መረጃ እንዲያገኙ ያስችላል" ብለዋል ።
የከተማውን የዕድገት ደረጃ የሚወስኑ መሠረት ልማቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ እንዲሄዱ ለማስቻል ዩኒቨርሲቲው የጥናትና የምርምር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር ዲሪባ አስታውቀዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የማሕበረሰብና አካባቢ ጥናት ማእከል ዳይሬክተር ዶክተር ደሣለኝ ዊርቱ ስለ መጽሐፉ ይዘትና ዝግጅት አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል ።
መጽሐፉ ለከተማው እድገት የሚረዱ ምቹ ሁኔታዎችና ሥጋቶችን አጣምሮ የያዘ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
"መጽሐፉ የከተማውን የልማትና እቅድ ፕሮግራም በማዘጋጀት በከተማው የልማት ሥራ ላይ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ሁሉ አስፈላጊውን መረጃ ለመስጠት ያግዛል " ያሉት ደግሞ የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ባህሩ ኤባ ናቸው ።
ዩኒቨርሲቲው የከተማውን ሕብረተሰብ ለማገዝ ስላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጾ የምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን የወለጋ ሙዝየምን በአዲስ መልክ በመገንባትና የቱሪዝም ማዕከል በማድረግ ለከተማው አስፈላጊውን ገቢ ለማስገኘት በዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች የተዘጋጀ ዲዛይን በመድረኩ ይፋ ተደርጎ ተመክሮበታል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የከተማውን መሠረታዊ መረጃ ከተበታተነ የመረጃ አያያዝ ወደ ተቀናጀና ለከተማው ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት በሚችል ሁኔታ ማቅረቡን አድንቀው ለጋራ ልማቱ ተሳትፏቸውን ለማጠናከር በጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
በውይይቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የተለያዩ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡