በክልሉ በነበረው የጸጥታ ችግር የባከነውን የግብርና ምርት ለማካካስ ለበጋ መስኖ ልማት ትኩረት ተሰጥቷል

69

አሶሳ፤ ህዳር 29 / 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የባከነውን የግብርና ምርት ለማካካስ ለበጋ መስኖ ልማት ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።

የበጋ መስኖን ጨምሮ የተለያየ  የግብርና  ልማትን ማሳደግ በሚቻልበት ዙሪያ  የምክክር መድረክ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ባበክር ከሊፋ በመድረኩ እንዳሉት፤ የአሸባሪውን ህወሓት ተላላኪዎች ከክልሉ ከማጽዳት ባለፈ የግብርና   ልማት ማጠናከር ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ እየተሰራ ነው።

በክልሉ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር አርሶ አደሮች ተረጋግተው መደበኛ የግብርና ስራቸውን እንዳያከናውኑ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ይህም ከፍተኛ የምርት መቀነስ ማሰከተሉን ጠቁመው፤ የታጣውን የግብርና ምርት ለማካካስ ለበጋ መስኖ ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የምክክር መድረኩም በግብዓት አቅርቦት እና ስርጭት፣ በበጋ ተፋሰስ ልማት፣ በእንስሳት መኖን ማሳደግ፣ እና በሌሎች የግብርና ምርታማነት በሚጨምሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉን አመልክተዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ከምክክሩ  በኋላ ለዕቅዱ አፈጻጸም ልዩ ትኩረት ሰጥው እንዲረባረቡ አቶ ባበክር አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የመስኖ ልማት ዳይሬክተር አቶ እስራኤል ኢዮብ በበኩላቸው፤  አርሶ አደሩ  መስኖን ተጠቅሞ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ የአስር ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በክልሉ በመስኖ የሚለማው መሬት መጠን ጭማሪ ቢያሳይም ካለው የውሃ ሀብት እና ለም መሬት አንጻር  ዝቅተኛ  መሆኑን ጠቁመዋል።

በምክክር መድረኩ  የተለያዩ  ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ  ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም