ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት በስልጣን ዘመኑ የተከበሩት በዓላት ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመከፋፈልና በመለያየት የራሱን ድብቅ ዓላማ ማስፈጸሚያነት ሲያውለው ነበር

ድሬዳዋ፤ ህዳር 29/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በስልጣን ዘመኑ የተከበሩት በዓላት ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመከፋፈልና በመለያየት የራሱን ድብቅ ዓላማ ማስፈጸሚያነት ሲያውለው ነበር ሲሉ ሲሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።

16ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዋዜማ በዓል ትላንት ምሽት በደመቀ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል፡፡

በዚህ ወቅት አፈ-ጉባኤው ባደረጉት ንግግር፤  አሸባሪው ህወሃት በስልጣን ዘመኑ የተከበሩት በዓላት ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመከፋፈልና በመለያየት የራሱን ድብቅ ዓላማ ማስፈጸሚያነት ሲያውለው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከለውጡ በኋላ የተከበሩት በዓላት በብዙሃነት ላይ የተመሠረተ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

በዘንድሮ በዓል ላይ እየተካሄዱ የሚገኙት ሲንፖዚዬሞች ይህንኑ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት የሚያጠነክሩ፣ የሀገርን ህልውና ለመጠበቅና ለማሻገር የተጀመሩ ተግባራት የሚጠናከሩ ይሆናል ብለዋል፡፡

የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ግንባር ተገኝተው እየሰጡ በሚገኙት የጀግንነት አመራር በጥምር ኃይላችን እየተመዘገበ ለሚገኘው ድል የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች አክብሮና ምስጋና ያቀርባሉ፤ ይህ ገድል ታሪክ ለምንጊዜም ያስታውሰዋል" ብለዋል፡፡

በተለይ አሸባሪው የህወሃት ወራሪ ቡድን ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ሀገርን ለማፍረስ የጀመረው ጦርነት በተባበረ ህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት በማክሸፍ የሀገርን ህልውና የማረጋገጡ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት፡፡

ኢትዮጵያን ለማዳን በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ መላው የጥቁር ህዝቦች ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው፤ አሁንም ይህ መተባበርና አንድነት መጠናከር አለበት ነው ያሉት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈቲህያ አደን፤ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ጥምር ጦር ድል እየተቀናጀ ባለበትና የተወረሩ አካባቢዎች ከአሸባሪው ነጻ እየወጡ በሚገኙበት ዋዜማ የዘንድሮ በዓል መከበሩ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ለማጎልበት ወሳኝ ምዕራፍ ይሆናል ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው፡፡

ትላንት ምሽት በተካሄደው የበዓሉ የዋዜማ ዝግጅት ላይ የኢፌድሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ፣ የክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች፣ አፈ-ጉባኤዎች፣ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ የመከላከያና የፀጥታ ተቋማት ከፍተኛ መኮንኖችና አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ኡጋዞችና አባገዳዎች፣ የሁሉም ክልሎች የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች ተሣታፊ ሆነዋል፡፡

የበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት ዛሬም በተለያዩ ዝግጅቶች ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም