በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ሴራ በማክሸፍ ለተረባረቡ ዳያስፖራና የኢትዮጵያ ወዳጆች መንግስት ምስጋና አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ሴራ በማክሸፍ ለተረባረቡ ዳያስፖራና የኢትዮጵያ ወዳጆች መንግስት ምስጋና አቀረበ
ህዳር 29/2014/ኢዜአ/ መንግስት ኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ሴራ ለማክሸፍ ለተረባረቡ የዳያስፖራ እና የኢትዮጵያ ወዳጆችን አመሰገነ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ፤ በሰጡት መግለጫ "ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያን ሕልውና የማስጠበቅ ዘመቻ ከፍተኛ ድል እየተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በጋራ ክንዳቸው የአገራችውን ክብርና ሉዓላዊነት እያስጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል።
አሸባሪውን ህወሓት እየተፋለሙ ካሉት በተጨማሪ ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ጫና የመፍጠር ሴራ በማክሸፍ ለተረባረቡ ዳያስፖራና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ መንግስት የላቀ ምስጋና አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ሠልፍ በመውጣት ከፈጠሩት ዲፕሎማሲያዊ ጫና ባሻገር ተፈናቃዮችን ለማገዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑም ገልጸዋል።
አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ ወደ አገር ቤት እንዲመጣ የተደረገውን ጥሪ ተከትሎ እንቅስቃሴው መጠናከሩንና የተለያዩ ተቋማትም ዳያስፖራውን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጋቸውን አክለዋል።
ኢትዮጵያ ባቀረበችው ጥሪ መሰረት በርካታ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት እንደሚመጡ ይጠበቃል።
አገራዊ ጥሪው ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ያለው ዘመቻ አካል በመሆኑ ወደ አገራቸው በመምጣት በተለይም የቱሪዝም ዘርፉን እንዲያነቃቁና የአገራቸውን ገጽታ እንዲገነቡም አቶ ከበደ ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በሳምንቱ ከተከወኑ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች መካከል በናይጄሪያ የአፍሪካ የሠላምና ጸጥታ ጉባኤ መካሄዱን፤ ኢትዮጵያም ጉባኤውን በሊቀ መንበርነት እየመራች መሆኑን ገልጸዋል።
በጉባኤው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተለያዩ አገራት በአፍሪካ የሚያደርጉት ያልተገባ ጫና እና ጣልቃገብነት ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በደቡብ ኮሪያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠላም ማስከበር ዓመታዊ ስብስባ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት አባል አገራት በአፍሪካ የሚያደርጉትን ኢ-መደበኛና ከቁጥጥር ውጭ ወታደራዊ ሰፈራን አዝማሚያ እና የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ሃይል እንዲወጣ የሚደረግ እንቅሰቀሴን ተገቢነት እንደሌለው ስለመግለጻቸውም አንስተዋል።
አሸባሪው ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ጅምላ ጭፍጨፋ፣ ኢ-ሠብዓዊ ድርጊቶች፣ ከፍተኛ የሀብት ውድመትና ዘረፋ ቢፈጽምም የሠብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን የሚሉ አካላት ድምጻቸው አልተሰማም ብለዋል።
በአንጻሩ መንግስትን በሠብዓዊ መብት ጥሰት እየከሰሱ መሆኑን ገልጸው፤ ከሠብዓዊ እርዳታ ጋር በተያያዘ የሚቀርበው መሰረተ ቢስ ክስ የፖለቲካ ፍላጎት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
በተያያዘም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ተፈናቃዮች የአስቸኳይ እርዳታ አቅርቦት የረድኤት ድርጅቶች እጃቸውን እንዲዘረጉ ጥሪ ቀርቧል።
መንግስትም ትግራይን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች ለተፈናቃይ ዜጎች አስቸኳይ እርዳታ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
-አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።