ቀጥታ፡

የአሸባሪው ህወሃት ቡድን የደሴ ሪፈራል ሆስፒታልን ሙሉ ለሙሉ ዘርፏል፤መውሰድ የማይችለውን ደግሞ አውድሟል

ህዳር 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሃት ቡድን የደሴ ሪፈራል ሆስፒታልን ሙሉ ለሙሉ ዘርፏል፤ መውሰድ የማይችለውን ደግሞ አውድሟል፡፡
በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተመራው የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት፣ ከደሴና ኮምቦልቻ በተጨማሪ በምሥራቅ ግንባር ባቲን፣ ቀርሳን፣ ገርባንና ደጋንን ነጻ ያወጣ ሲሆን በሐርቡ ግንባር ደግሞ ቃሉ ወረዳን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩ ይታወቃል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በወረራ ይዟቸው በነበሩ በእነዚህ አካባቢዎች የመንግስትና ግለሰብ ንብረቶችን ዘርፏል፤ መውሰድ ያልቻላቸውን ደግሞ አውድሟል፡፡

የሽብር ቡድኑ በተለይ የህዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት የፈጸመ ሲሆን፤ ከእነዚህ ተቋማት መካከል የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ተጠቃሽ ነው፡፡

ኢዜአ በሆስፒታሉ ተገኝቶ ባደረገው ቅኝት ሆስፒታሉ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት መድረሱን ተመልክቷል፡፡

የሆስፒታሉ ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ጌታቸው መታፈሪያ እንዳሉት፤ አሸባሪ ቡድኑ ሆስፒታሉን ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ መድሃኒትን ጨምሮ ትልልቅ የህክምና ማሽነሪዎችን ዘርፎ መውሰዱን ገልጸው፤ በተለይ በቅርቡ ተመርቆ በሆስፒታሉ ውስጥ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረውን የኦክስጅን ማምረቻ ሙሉ ለሙሉ ዘርፈው መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በሆስፒታሉ በቅርቡ ተገዝተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ አልጋዎችን ደግሞ አውድሟቸዋል ነው ያሉት፡፡

መውስድ ያልቻሏቸውን መድሃኒቶች ጥቅም እንዳይሰጡ አድርጎ ማውደሙንም ተናግረዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ የሆስፒታሉን ጀኔነተር ነዳጅ ዘርፎ በመውሰድና ሆስፒታሉ ነዳጅ እንዳያገኝ በመከልከል መትረፍ የሚችሉ ህመምተኞች እንዲሞቱ ማድረጉንም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም