ቀጥታ፡

እየተመዘገበ ያለው ድል በኢትዮጵያ ላይ የሚነሱ ጠላቶች ሁሉ ተሸንፈውና ተዋርደው የሚመለሱ መሆኑን ያረጋገጠ ነው

ህዳር 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ“ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” እየተመዘገበ ያለው ድል በኢትዮጵያ ላይ የሚነሱ ጠላቶች ሁሉ ተሸንፈውና ተዋርደው የሚመለሱ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ሲሉ በግንባር የተገኙ አርቲስቶች ተናገሩ።
የአሸባሪውን ህወሃት ወረራ ለመመከት እየተደረገ ባለው የህልውና ዘመቻ የመላ የኢትዮጵያዊያን ተሳትፎና አንድነት ይበልጥ ተጠናክሮ የታየበት፣ በጋራ ክንድ ጠላት እየተመታ ያለበት ልዩ አጋጣሚ መሆኑንም ገልጸዋል።

በግንባር አግኝተን ያነጋገርናቸው አርቲስት ተሾመ አየለ (ባላገሩ)  እና አርቲስት ሚካኤል ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን አንድነታችን ይበልጥ እየተጠናከረ በመምጣቱ ሊበትነንና በህልውናችን መጥቶ ሊበግረን የሚችል ጠላት የለም ብለዋል።

“ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያን ህልውና የማስጠበቅ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ የሚነሱ ጠላቶች ሁሉ በቁርጥ ቀን ልጆቿ ተዋርደውና ተሸንፈው የሚመለሱ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

"ኢትዮጵያን እናፈራርሳለን" በማለት የተነሱት አሸባሪና ባንዳዎች እንዲሁም የውጭ ጠላቶች ሳይሳካላቸው ሐፍረት እየተከናነቡ መሆኑን አርቲስት ተሾመ አየለ (ባላገሩ) ይናገራል።

በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ተጋድሎ እየተገኘ ያለው ድል ኢትዮጵያን ዳግም ከፍ ያደረገ ልዩ የታሪክ አጋጣሚ መሆኑንም ጠቅሷል።

መሆኑም ለኢትዮጵያ ህልውና እየተዋደቁ ለሚገኙት የጸጥታ ሃይሎች ሁላችንም ልንደግፋቸውና ልናግዛቸው እንዲሁም አብረናቸው ልንሰልፍ ይገባል ነው ያለው።

በጦርነቱ የተጎዳውን ኢኮኖሚ መልሶ ለማነቃቃት በሰአት ሳንገደብ የምንሰራበት ሌላው የህልውናችን ጉዳይ ነው ሲልም ባላገሩ ተናግሯል።

አርቲስት ሚካኤል ሚሊዮን በበኩሉ መከላከያ ሰራዊቱና ሌሎች የጸጥታ አካላት የሚከፍሉት መስዋዕትነት ለሀገራቸው ያላቸውን ጽኑ ፍቅር የሚያሳይ በመሆኑ ሁላችንም አብረናቸው ልንሰለፍ ይገባል ብሏል።

የኢትዮጵያ ጥምር ሃይል ለአገሩ ህልውና ሲል በጀግንነት እየተፋለመ ጠላትን በየግንባሩ እያፀዳ ያለበት መንገድ የሚደነቅ መሆኑንም ጠቅሷል።

ኢትዮጵያን በወረራ ለማንበርከክ የሞከሩት የጥፋት ሃይሎች ሁሌም የማይሳካላቸው መሆኑን በጋራ ክንዳችን አረጋግጠናል ብሏል።

ኢትዮጵያ የተደቀነባትን የህልውና አደጋ በመመከት ያስመዘገበችው ድል ለመላ አፍሪካዊያን ሌላኛው የአሸናፊነት ተምሳሌት ነው ሲልም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም