ቀጥታ፡

በሰብአዊ መብት ጥበቃ ስም በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ ሙከራን ኢትዮጵያ አትቀበልም

ህዳር 29ቀን 2014 (ኢዜአ) በሰብአዊ መብት ጥበቃ ስም በውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግን ሙከራ ኢትዮጵያ አትቀበልም ሲሉ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ አስታወቁ፡፡

ዶ/ር ጌዲዮን መቀመጫቸውን በጄኔቫ ላደረጉ የአፍሪካ አምባሳደሮች ቡድን በኢትዮጵያ ስላለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያም በኢትዮጵያ ስላለው ሰብአዊ መብት ጉዳይ አስመልክቶ በአለም አቀፍ ሚዲያዎች የሚስተጋቡት ውንጀላዎች እና አደገኛ ንግግሮችን ምንም አይነት እውነትነት የሌላቸውን የሰብአዊ መብትን ጉዳይ እንደ ፖለቲካ መሳሪያ ለመጠቀም የሚፈልጉ አገራት የሚያሰራጩት መሰረተ ቢስ ውንጃላ ናቸው።

በዚህም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሰብአዊ መብት ጥበቃን ሽፋን በማድረግ በውስጥ ጉዳይ ለመግባት የሚደረግ ሙከራን ኢትዮጵያ አትቀበልም ብለዋል። እንደዚህ አይነት ጣልቃ ገብነት የሰብአዊ መብት አጀንዳዎችን ለማራመድ የሚደረገውን እውነተኛ ጥረት የሚጎዳ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ባጣኑት የሪፖርት ግኝቶች ላይ መንግስት አንዳንድ ጥርጣሬዎች ቢኖሩትም የቀረቡት የውሳኔ ሃሳቦች ሙሉ በሙሉ በመቀበል በፍጥነት እንዲተገበሩ ለማድረግ የሚኒስትሮች ግብረ ሃይል ማቋቋሙን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግስት በሃይል ለማስወገድ የሰብአዊ መብትን በሽፋን የመጠቀም የሴራ ፍላጎት ኢትዮጵያ እንዳማትቀበል አብራርተውላቸዋል፡፡

ይህንንም የሚያደርጉት የአሸባሪ ቡድኖችን የሀገር ክህደት በመፈጸም ወንጀል እንዲሰሩ በማድርግ መሆኑን በአጽእኖት ገልጸዋል።የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ የሚያሳስባቸው ወገኖች ካሉ መስራትና መተባበር ያለባቸው በዘርፉ እምርታን ለማስመዝገብ ከሚጥረው የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሊሆን ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም