ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ እንዲቻል በምርጫ ቦርድ ተቋማዊ አሰራር ላይ ለውጥ ማድረግ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ ነሐሴ 17/2010 በኢትዮጵያ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲረጋገጥ በሀገሪቱ ምርጫ አስፈፃሚ መስሪያ ቤት ላይ ተቋማዊ ለውጥ ማድረግ እንደሚገባ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ገለፁ። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ተቋማዊ ለውጥ ለማድረግ ከሀገር አቀፍና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር  በጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ "ተቋማዊ ለውጥ ለቀጣይ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ ከሀገር አቀፍና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ምክክር አካሄዷል። በምክክር መድረኩ ላይ የፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በሰጡት አስተያየት የምርጫ ቦርድ ተቋማዊ አደረጃጀት ተፈትሾ የማሻሻያ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል። የምርጫ አስፈፃሚዎች አቅምና ገለልተኝነት መረጋገጥ እንዳለበት ያሳሰቡት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከምርጫ ጋር የተያያዙ የህግ ማዕቀፎችም ተፈትሸው ሊሻሻሉ ይገባል የሚሉ ሃሳቦችንም አንሸራሽረዋል። ከአረና ትግራይ ፓርቲ አቶ ካህሳይ ዘገየ እንዳሉት የቦርዱ አመራር ከኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ለህሊናቸው የሚሰሩ ምሁራንም ሊያካትት ይገባል፡፡ ከመላው ኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት ድርጅት አቶ ሙሉጌታ አበበ ደግሞ “ለምርጫ ቦርድ የሚያስፈልገው ሪፎርም ሳይሆን ፈርሶ መሰራት ነው፡፡” የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ  አባላቱ የምርጫ ቦርድ የሚለው ስያሜ ወደ ኮሚሽን ይቀየር የሚል ሀሳብም አንስተዋል፡፡ በሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሣሚያ ዘካሪያ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ እያካሄደች ካለው ለውጥ ጋር ራሱን ለመቀየር የሚያስችለውን ጥረት ጀምሯል ብለዋል። ይህንን ጥረት የተሳካ ለማድረግም የተፎካካሪ ፓርቲ አካላት የለውጡ ባለቤት እንዲሆኑ በሚችሉበት መንገድ ምክክር እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። መንግስት የጀመረውን የተሃድሶ ጉዞ በተሟላ ሁኔታና በዘላቂነት ማስቀጠል የሚቻለው የአገሪቱን ሰላምና ልማት ከማረጋገጥ ባሻገር የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት እንደዚሁም በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ብቻ የመንግስት ስልጣን የሚያዝበትን አሰራር በመዘርጋት ነው ብለዋል። ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ ለማካሄድ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ለማድረግ ግንዛቤ መፍጠርና የተቋሙን አደረጃጀትና የውስጥ አሰራር በመፈተሽ ችግሮቹን መለየት ያስፈልጋል ሲሉም ወይዘሮ ሳሚያ አብራርተዋል። ምርጫ ቦርድ ውስጣዊ አቅሙን ለማጠናከር በሚተጋበት ወቅት የመንግስት ትኩረትና ድጋፍ እንደሚያስፈልገውም ጭምር ነው የቦርዱ ሰብሳቢ አምባሳደር ሣሚያ ዘካሪያ የሚገልፁት። በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ከተጀመረበት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት 27 ዓመታት አምስት ጠቅላላ ምርጫዎች ተካሂደዋል። ይሁን እንጂ ባለፉት ሁለት ጠቅላላ ምርጫዎች በየደረጃው በሚገኙ ምክር ቤቶች የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተሳታፊ አልነበሩም ሲሉ ወይዘሮ ሳሚያ ገልፀዋል። ይህም የምርጫውንና የምርጫ አስፈፃሚ ተቋሙን ተዓማኒነት አሳጥቶታል በማለት። በመሆኑም የምርጫ ቦርድ ተቋማዊ አሰራር ላይ ለውጥ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለፁት ሰብሳቢዋ በዚህም በሀገሪቱ ወደፊት የሚካሄዱ ምርጫዎች ነጻነትና ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ አስተዋፆ ይኖረዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም