በዓሉ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ ደግም ቃላችን የምናድስበት ነው - ተሳታፊዎች

94

አዳማ፤ ህዳር 28/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔር ፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል የሀገራችንን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ ዳግም ቃላችን የምናድስበት ነው ሲሉ በአዳማ ከተማ አስተዳደር የክብረ በዓሉ ተሳታፊዎች ገለጹ።

16ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በአዳማ ከተማ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ ተከብሯል።

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል የሀገር ሽማግሌ ሃጂ ሁሴን ዑስማን እንዳሉት በዓሉ የሀገራችንን  ሉዓላዊነትን ለማስከበር ዳግም ቃላችንን የምናድስበት ነው።

በአሸባሪው ህወሓት ያጋጠመን ወቅታዊ የሕልውና ስጋት በቅርቡ በድል እንደሚቋጭ ገለጸው፣ ለዚህ ደግሞ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ሁላችንም በየፊናችን ግንባር ካለው መሪያችንና የፀጥታ ሀይላችን ጎን መቆም አለብን ብለዋል።

የዘንድሮውን በዓል የምናከብረው መሪያችን በጦር ግንባር ከፍተኛ ገድል እየፈፀመ ባለበት ወቅት በመሆኑ በሰጠን ልዩ ስሜትና ደስታ እኛም ከጎኑ መሆን አለብን ያሉት ደግሞ አቶ ከበደ ናቸው።

ወይዘሮ ፋቲማ ሳይድ እንዳሉት ሁላችንም ለአካባቢያችን ሠራዊት ሆነን ሰርጎ ገቦችና የጠላት አሉባልታ የሚነዙ ተላላኪዎችን በመከላከል መሪያችንን በማገዝ ሉዓላዊት ሀገር ለልጆቻችን ማውረስ አለብን።

በመደረኩ ላይ የመወያያ ጽሑፊ ያቀረቡት አቶ አበበ ጉተማ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የውጭ ወራሪን በአድዋ ጦርነት ድል አድርጋ ለጥቁር አፍሪካውያን የነፃነት መነሻ የሆነች ሀገር ናት ብለዋል ።

እንደ አቶ አበበ ገለጻ በዚህ ተምሳሌትነት ሁላችንም ብሔር ብሔረሰቦች አንድነታችንን በማጠናከር የኢትዮጵያን ጠላት ማሳፈር ይገባናል።

የዘንድረውን በዓል ልዩ የሚያደርገው ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በጠላቶቻችን የተቃጣብንን ጦርነት ለመቀልበስ በግንባር ዘምተው አመርቂ ድል እያስመዘገቡ ባሉበት ወቅት መከበሩ ነው ያሉት ደግሞ የከተማው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሂንሴኔ ሙሐመድ ናቸው።

የከተማዋ ነዋሪዎችም የሀገር ህልውናን ለመታደግ በሀብታቸው፣ በእውቀታቸውና በጉልበት ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም እያሳዩ ያሉትን ድጋፍና ደጀንነት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ሙሐመድ ጉዬ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራልዝምን እንደ ሽፋን በመጠቀም የቡድኑን የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሲያስጠብቅ ቆይቷል።

በሀገራችን ትክክለኛ "ህብረ ብሔራዊ ፌዴራልዝም እውን እየሆነ ያለው በለውጡ መንግስት ነው" ያሉት አቶ ሙሐመድ ህወሓትና ለውጡ ያልተዋጠላቸው የውስጥና የውጭ ግብረ አበሮቹ  ጦርነት የከፈቱትም ጥቅማቸው ስለቀረባቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

ለዚህም ህዝቡ በሁሉም መስክ የጀመረውን የሀገረ መከላከያ ሰራዊትን የመደገፍና የማጠናከር ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም