አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች አምራች ኢንዱስትሪዎችን አውድሟል

88

ህዳር 28/2014 አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አማራና አፋር አካባቢዎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ኃይሎች የወደሙ አምራች ኢንዱስትሪዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ በዚህን ወቅት እንዳሉት፤ የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

በጨርቃጨርቅ፣ ኬሚካል፣ ቆዳ፣ ብረታብረት፣ በምግብና ምግብ-ነክ ዘርፎች በተሰማሩ ከጥቃቅን እስከ ከፍተኛ አምራች ተቋማትን ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ነው ያሉት፡፡

የሽብር ቡድኑ በኢንዱስትሪ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ማሽነሪዎችን ነቅሎ መውሰዱንና ቀሪዎችን ደግሞ ማውደሙን ገልጸዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የሚመራው የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ነጻ ባወጣቸው እንደ ኮምቦልቻ ባሉ የኢንዱስትሪ ኮሪደሮች አሸባሪ ቡድኑ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

አሸባሪ ቡድኑ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች መዋለንዋያቸውን አፍስሰው እየሰሩባቸው በነበሩና ከ50 እስከ 800 ዜጎች የሥራ እድል በፈጠሩ ማምረቻ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱንም አንስተዋል፡፡

እስካሁን በደረሰው መረጃም በኮምቦልቻና ደሴ አካባቢዎች 32 እንዲሁም በአፋር ክልል 4 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙንም ነው የተናገሩት፡፡

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ውድመቱን በዝርዝር ለመለየትና መልሶ ሥራ ለማስጀመር ውድመቱን  የሚያጠና የባለሙያዎች ቡድን ወደ ስፍራው እንደሚያቀናም ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ እስካሁን በደረሰው መረጃ መሰረት አሸባሪ ቡድኑ 10 የምግብና ምግብ-ነክ ፤ 11 የቆዳና ጨርቃጨርቅ፤ 3 የብረታብረት፤ 11 በአግሮ ፕሮሰሲንግ እና 10 የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ላይ ውድመት አድርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም