አሸባሪው ህወሓት ዳግም የሀገርና የሕዝብ ስጋት እንዳይሆን በማድረግ ሁሉም ወደ ልማት መዞር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት ዳግም የሀገርና የሕዝብ ስጋት እንዳይሆን በማድረግ ሁሉም ወደ ልማት መዞር አለበት
ደብረ ታቦር፣ ህዳር 28/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ዳግም የሀገርና የሕዝብ ስጋት እንዳይሆን በማድረግ ሁሉም ወደ ልማት መዞር እንዳለበት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን አስገነዘቡ፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው በደብረ ታቦር ከተማ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተካሄደ ውይይት ላይ እንዳሉት አሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው፡፡
ምዕራባዊያን ተላላኪ መንግስት መስርተው ሀብታችንን ለመዝረፍና ሉዓላዊነታችን ለመዳፈር ቢሞክሩም በኢትዮጵያዊያን የጋራ ክንድ አልተሳካላቸውም፤ ወደፊትም አይሳካላቸውም ብለዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ በአማራና በአፋር ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች የእምነት ተቋማትን አርክሷል፤ በጅምላ ጨፍጭፏል፤ ንብረትም ዘርፏል፤ ህብረተሰቡን አጎሳቁሏል ሲሉ ገልፀዋል።
ለእምነት ተቋማት እንኳ ክብር የሌለውን የሽብር ቡድኑ በተባበረ ክንድ የለመደው ዋሻ ሳይሆን ዳግም ስጋት በማይሆን መልኩ "የዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነትን" በማጠናቀቅ የልማትና ብልፅግና ጉዟችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
ወጣቱም አንድነቱን ጠብቆ መከላከያና ልዩ ኃይሉን ተቀላቅሎ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በማስከበር የአባቶቹን ታሪክ በመድገም የጥቁር ህዝቦችን የጀግንነት ተምሳሌትነት በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ደጀኔ እንዳሉት የሽብር ቡድኑ ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች የሐይማኖት ተቋማትን ከማውደሙም በላይ መፀዳጃ ጭምር በማድረግ ማርከሱ የአስነዋሪ ተግባሩ መገለጫ ነው።
የሽብር ቡድኑንና ጋላቢዎቹን የደቀኑትን ወቅታዊ የሕልውና አደጋ በአጠረ ጊዜ በድል ለማጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
የሽብር ቡድኑ በሰራው የከፋፍለህ ግዛና የሴራ ፖለቲካ የኢትዮጵያን ህዝብ በዘርና በሐይማት የተከፋፈለው ቢመስለውም አንድነቱን ጠብቆ ሀገር የመበተን እኩይ ዓላማውን እያመከነ ነው ብለዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ወጣቱ እያለ ኢትዮጵያን ለማዋረድና ለመበተን ያደረገው ሙከራና የፈፀመው በደል መቼም ቢሆን ሊረሳ አይችልም ያለው ደግሞ ወጣት ጌታሰው ሙጨ ነው።
ቡድኑን ዳግም የሀገር ስጋት እንዳይሆን የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ተቀላቅሎና ወታደራዊ ሳይንሱን ተምሬ የኢትዮጵን ሉዓላዊነት ለማስቀጠል ቆርጦ መነሳቱን ገልጿል፡፡
በድምጻችን በመረጥነው መንግስት እንጅ ምዕራባዊያን በሚያስቀምጡልን ተላላኪ የአሽንጉሊት መንግስት የማንመራ ኩሩ ኢትዮጵያዊ መሆናችንንም በተግባር እናሳያቸዋለን ብሏል፡
ሌላው ወጣት ሙሉዬ ይግዛው በበኩሉ አሸባሪው ወራሪ ኃይል ከአማራና ከአፋር የዘረፈውን ሀብት ለማስመለስ እስከ ህይወት መስዋእትነት ጭምር ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ብሏል፡፡
ከሐገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ ክንዴ አለሙ እንዳሉት ህብረተሰቡ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ግንባር የሚሄዱት መርቆ ከመሸኘትና ፀሎት ከማድረግ ባለፈ የደጀንነት ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
በውይይቱ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የደብረ ታቦር ከተማ አመራሮች፣ ነዋሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።