ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያዊያን የደስታ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያዊያን የደስታ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 28 /2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሸዋ፣ ከሚሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ ባቲ እና አካባቢው ከህወሃት የሽብር ቡድን ወራሪ ኃይል ነፃ መውጣታቸውን ተከትሎ ለመላ ኢትዮጵያዊያን የእንኳን ደስ ያላቹህ መልዕክት አስተላለፉ።
የአገር መከላከያ ሰራዊት ባካሄደው ኦፕሬሽን የሸዋ፣ የከሚሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ባቲን እና አብዛኛው ደቡብ ወሎ ከሽብር ቡድኑ ወራሪ ኃይል ነፃ ማውጣታቸውን አውጥቷል።
በቀሩት የሰሜን ወሎ አካባቢዎችም እየተካሄደ ያለው ኦፕሬሽን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
እስካሁን የተገኘው ድልም በጠላት ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ በማድረስ በርካታ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች መማረካቸውን ጠቁመዋል።
የወገን ጦርን የሰነዘረውን ከባድ ምት ጠላት መቋቋም አለመቻሉንም አመላክተዋል።
የእኛ ፍላጎት ሰላምና ብልጽግና እንዲመጣ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ጦርነት ተገደን፣ ተገፍተንና ለምነን ሲያቅተን የገባንበት ነው ብለዋል።
በእውር ድንብር የገባው የሽብር ቡድኑ ወራሪ ኃይልም የዘረፈውን ንብረትና የሰው ኃይሉን ይዞ መውጣት እንዳይችል ባለፉት ሁለት ቀናት አመርቂ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
የአሸባሪ ታጣቂ ከተለያዩ ተቋማት የዘረፈውን ንብረት ይዞ እንዳይወጣ ተደርጎ በመመታቱ ተበታትኖ እየሸሸ ስለመሆኑም አስታውቀዋል።
ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም እየተገኘ ላለው ድል የእንኳን ደስ ያላቹህ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በገድልና ጀግንነት የምትታወቀው ኢትዮጵያም የማትሸነፍ መሆኗን ጠቅሰው ኢትዮጵያ አንገቷን በነፃነት ቀና አድርጋ እንድትሄድ የወረስነውን አሸናፊነት ለልጆቻችን ማስቀጠል ይገባናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወታደርም በቃላት የማይገለጽና የማይታመን ጀግንነትን ተላብሶ ታሪክ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።