ቀጥታ፡

የውጭ ጣልቃ ገብነትን በፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ለመመከት አፍሪካውያን በጋራ ሊቆሙ ይገባል

እንጅባራ፤ ህዳር 28/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን የውጭ ጣልቃ ገብነት በፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ለመመከት አፍሪካውያን በጋራ መቆም እንዳለባቸው የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለፁ።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር ስሜነህ ቢረስ እንዳሉት በአፍሪካ አገራት ላይ የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት እየጨመረ መጥቷል።

ይህም የአፍሪካ አገራት ያላቸውን ሃብትና ጸጋ አልምተው አገራቸውን እንዳያሳድጉና ህዝባቸውን ተጠቃሚ እንዳያደርጉ እንቅፋት እየፈጠረ መምጣቱን ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስቆም አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራትና አሜሪካ እያደረሱት ያለውን ጫና ለእዚህ እንደ አንድ ማሳያ አቅርበዋል።

በሊቢያና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ላይ የተፈጸመውን ሴራ ያስታወሱት መምህሩ፣ አሁን ኢትዮጵያን በእጅ አዙር የቅኝ ግዛት ስር ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጫና መከላከል ለኢትዮጵያ ብቻ መተው እንደሌለበት ገልጸዋል።

"ለእዚህም የቀጠናው አገራት በአንድ ላይ በመቆም የምዕራባዊያንን ጫና ለመቋቋም በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል" ብለዋል።

ኢትዮጵያን ተባብሮ ለማንበርከክ የሚደረገው የምዕራባውያን ጫና ለአፍሪካ አገራትም ስለሚተርፍ አገራት የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል በጋራ እንዲጸኑ አስገንዝበዋል።

"ለዚህም እንደ ኢጋድና የአፍሪካ ሕብረት ያሉ አህጉራዊ ድርጅቶችን በመጠቀም የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን በማጎልበት ጫናዎችን ለመቋቋም መስራት ይኖርባቸዋል" ብለዋል መምህሩ።

አሸባሪው ህወሓትን በመደገፍ ከኢትዮጵያ ጥቅም በተጻራሪ የተሰለፉ የውጭ ሃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ የተጀመረውን የ "# ኖ ሞር" ንቅናቄ አፍሪካዊያን በያሉበት እንዲደግፉም አስገንዝበዋል።

የዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሀብት መምህር አቶ ካሱ ኃይሉ በበኩላቸው፣ ምዕራባዊያን የራሳቸውን ፍላጎት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለመጫን የንግድ ማዕቀብ በማድረግና በተለያየ መንገድ እያስፈራሩ መሆኑን ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያ መቼውንም ለውጭም ሆነ ለውስጥ ጠላት ተንበርክካ አታውቅም" ያሉት ምሁሩ፣ የአፍሪካ አገራትም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በምታደርገው ጥረት ከኢትዮጵያ ጎን እንዲሰለፉ ጠይቀዋል።

ለዕርዳታ፣ ብድር እና ለንግድ ተብሎ ሉዓላዊነት ሊገሰስ አይገባም ያሉት መምህሩ፣ መንግስትም የኢትዮጵያ ሉአላዊነት ከሚቀበሉ አገራት ጋር ግንኙነቱን ማጠናከር ላይ እንዲያተኩር መክረዋል።

የህዝቡን አንድነትና ትብብርን በማጠናከርም እንደ ህወሓትና ሸኔ ያሉ አሸባሪ ድርጅቶችን በግንባር ለማሸነፍ የተጀመረው ሁሉን አቀፍ ትብብርም እንዲጠናከርም አስገንዝበዋል።

በኢኮኖሚ እንቅስቃሴውም የዘርፉ የአገር ውስጥ ምርታማነትን በመጨመር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካትና ከውጪ የሚገቡ የቅንጦት ዕቃዎችን በመቀነስ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ተከታታይ ስራዎችን መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም