ከህወሓት ወራሪ ሃይል ነጻ በመውጣታቸው መደሰታቸውን የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

31

ደብረ ታቦር ህዳር 27/2014 (ኢዜአ) የላሊበላ ከተማን ለማፍረስ ከመጣውና በጭካኔ ተግባሩ ከሚረካው የህወሓት ወራሪ ኃይል ነፃ በመውጣታቸው መደሰታቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በአሸባሪው ህወሓት ከተፈጸመባቸው የግፍ ወረራነጻ የወጡት ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በችግሩ ይበልጥ መተዛዘንን፣ መረዳዳትንና አብሮነትን መማራቸውን ተናግረዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አስር አለቃ ውበት አሰፋ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት ከተማቸውን ሊያወድም የመጣ እርኩስ መንፈስ የተጠናወተው ነው፡፡

የሽብር ቡድኑ በከተማዋ በቆየባቸው ጊዜያት መልከ ብዙ ሰቆቃ ያደረሰባቸው ከመሆኑም በላይ በላሊበላ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዝርፊያና ውድመት ማድረሱን ገልጸዋል።

"የአሸባሪው ህወሓት ግፍና በደል የሚረሳ ባይሆንም መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይሉ፣ ሚሊሻ፣ ፋኖና ህዝባዊ ሠራዊቱ ከዚህ አረመኔያዊ ቡድን ነጻ ስላወጡን ተደስተናል" ብለዋል።

አካባቢያቸው አሁን ከወራሪው ሀይል ነጻ በመሆኑ ከስቃይና ከጭቆና ቀንበር መላቀቃቸውንም ነው የተናገሩት።

ከሽብር ቡድኑ ዘረፋና ስርቆት ደብቀው ያስቀሩትን ምግብ እርስ በእርስ ተካፍለው በመብላት ክፉውን ጊዜ ለማለፍ እንደቻሉም አስር አለቃ ውበት ተናግረዋል።

"ችግሩ አንድነታችንን ከመጠናከሩ ባለፈ መተጋገዝንና መተዛዘንን ተምረንበታል" ብለዋል፡፡

"አሸባሪው የህወሓት ቡድን የሰው ልጅ በዚህ ዘመን ይሰራዋል ተብሎ የማይጠበቅ ግፍ በንፁሀን ላይ ፈፅሟል" ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ቀሲስ ሀብታሙ ሰጥአርጌ ናቸው፡፡

"ለአራት ወር በቆየበት ላሊበላ ከተማቸው ጨቅላ ህጻናትና አረጋዊያን ሳይቀሩ ገድሏል፤ የላሊበላ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያውንም አውድማል፤ ንብረት ዘርፏል።" ብለዋል።

"ጥፋት ግብሩ በመሆነው በእዚህ አሸባሪ ቡድን ተሰቃይተናል፤ መከራና እንግልትም ደርሶብናል" ሲሉም አክለዋል፡፡

አሁን ከጭቆና ቀንበር ነጻ በመውጣታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፣ ሠራዊቱን በመደገፍ የኢትጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የቅዱስ ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ጽዬስላሴ መዝገቡ በበኩላቸው በጦርነቱ ምክንያት አገልግሎት መስጫ ተቋማት በመውደማቸው ህብረተሰቡ ለከፍተኛ ችግር መዳረጉን ተናግረዋል።

አስተዳዳሪው እንዳሉት ወላድ እናቶች በሕክምና እጦት ህይወታቸው እንዳያልፍ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ ቤተ ክርስቲያኗ የበኩሏን እገዛ ብታደርግም የመድሃኒት፣ የነዳጅና የኦክሲጅን እጥረት ተከስቷል።

በወራሪው ቡድን ያሳለፉት የመከራ ወራት ዛሬ አልፎ በመመልከታቸው ፈጣሪን ያመሰገኑት አስተዳዳሪው፣ ከተማዋን ለቆ ያልወጣው የህብረተሰብ ክፍል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ማለፉን ተናግረዋል።

በወረራ ጊዜ ሁሉም ያለውን ምግብና ገንዘብ በማምጣት እርስ በርስ ተዛዝኖና ተካፍሎ እየበላ ችግሩን ማለፉን ተናግረዋል፡

"ያሳለፍነው አራት ወር ከአራት ዓመት ቢበልጥብንም መተዛዘንን፣ መረዳዳትና አብሮነትን አስተምሮናል" ብለዋል።

መንግስት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ሥራ እንዲጀምሩ ማድረግና ለህብረተሰቡ የእለት ደራሽ ምግብ በአስቸኳይ በማቅረብ ዜጎችን ከሞትና ከርሃብ እንዲታደግም ጠይቀዋል፡፡

ጀግናው መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻው፣ ፋኖውና ህዝባዊ ሠራዊቱ አሸባሪውን ህወሃት አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የተለያዩ ከተሞችን ነጻ እያወጣና ወደ ፊት እየገሰገሰ ስለመሆኑ መንግስት መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም