በደቡብ ክልል ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

36

ሐዋሳ፤ ህዳር 27/2014(ኢዜአ) በደቡብ ክልል ባለፉት አራት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የክልሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባባሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ሚልክያስ እስራኤል ለኢዜአ እንደገለጹት ገንዘቡ ከክልሉ ነዋሪዎች  በስጦታና በቦንድ ግዥ የተሰባሰበ ነው።

ይህም  ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው ገቢ ጋር ሲነፃጸር 30 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አመልክተዋል።

የመጀመሪያውና ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የሚታዩ ኢ-ፍትሃዊ  አካሄዶች በዜጎች ላይ ቁጭትንና መነሳሳትን በመፍጠሩ ለግድቡ የሚደረገው ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ማድረጉን ጠቁመዋል።

የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ተግባራትን በማከናወን እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ 200 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ህብረተሰቡ  የጀመረውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲገፋበት ጠይቀዋል።

የግድቡ መጠናቀቅ በሀገር ዕድገት ላይ የሚኖረው ፋይዳ የላቀ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ክልል የብሄረሰቦች ምክር ቤት ሠራተኛ አቶ ዳርሰማ አንሳ ናቸው።

ይሄን በመረዳትም ከሚያገኙት ወርሃዊ ደመወዝ ላይ በመቀነስ  ለአምስተኛ  ጊዜ  ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የግድቡ ግንባታ አጋጥሞት ከነበረው መጓተት  ወጥቶ በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ መገኘቱ  እምነት እንዲያድርባቸው እንዳደረገና መነሳሳት እንደፈጠረላቸው አመልክተዋል።

''በውጭ ኃይሎች  በተደጋጋሚ ጊዜ እየደረሰ ያለው ጫና ተስፋችንን እንዳያጨልም ለግድቡ ግንባታ የምናደርገውን ድጋፍ ለአፍታም መዘንጋት የለብንም'' ብለዋል።

የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ዘለቀ ከበደ በበኩላቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ የሁሉንም አካል ተሳትፎ እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።

መንግስት ለግድቡ ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ በሀገር ውሰጥና በውጭ ሀገር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ አማራጮችን መዘርጋቱን የገለጹት አቶ ዘለቀ ሁሉም አካል የነቃ ተሳትፎ በማድረግ አሻራውን ሊያሳርፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።

 ''እኔን ጨምሮ መላው ዜጋ ካለምንም ጎትጓች በቁጭት ስሜት ግድቡን እንደጀመርነው ለማጠናቀቅ እንትጋ'' ብለዋል።

ባለፉት  ዓመታት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቦንድ ግዢ እና በስጦታ  ከ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ  ድጋፍ መደረጉ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም