ቀጥታ፡

የትምህርት ስልጠና ፍኖተ ካርታው ለኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራትን ዓላማ ያደረገ ነው-ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ

አዲስ አበባ ነሀሴ  17/2010  በአሁኑ ወቀት ለውይይት የቀረበው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ኢትዮጵያ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለመሸጋገር የምትፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራት  የሚያስችል መሆኑን የፍኖተ ካርታው ዝግጅት አስተባባሪ ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ ገለፁ። ለመጪው 15 ዓመት የትምህርት ሴክተሩ እንዴት መመራት አለበት የሚል ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ የትምህርት ባለሙያዎች እየመከሩበት ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የፍኖተ ካርታው ዝግጅት አስተባበሪ ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ እየተዘጋጀ ያለው ፍኖተ ካርታ ከትምህርት ተቋማት "ብዛት ይልቅ ለትምህርት ጥራት ትኩረት የሰጠ ነው" ብለዋል። አሁን ያለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዛት በቂ ባይሆንም ለጥራት ቅድሚያ መስጠት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ ፍኖተ ካርታው የትምህርት ጥራትን የሚያጎለብቱ ከሰነዶች፣ ከመስክ ጥናትና ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ የተገኙ ግብዓቶች እንደተቀመሩበትም ገልፀዋል። በተለይም በከፍተኛ ትምህርት በኩል "ከቁጥር ይልቅ ለጥራት ትኩረት መደረግ አለበት" ያሉት ፕሬፌሰሩ፤ ጥራትን ለማሻሻል የላቦራቶሪና የሰርቶ ማሳያ ግብዓቶች በተሟላ መልኩ እንዲኖርና እነዚህ ካልተሟሉ ከፍተኛ ትምህርት መክፈት አያስፈለግም የሚል ሀሳብ ተካቶበታል ብለዋል። ፍኖተ ካርታው አሁን ስራ ላይ ያለውን በ1994 ዓ.ም የተዘጋጀውን የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ እንደሚያሻሽልም ገልፀዋል። ተማሪዎች ከመሰናዶ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት መስክ ምርጫ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ እንዲሆንም ይመከራል ብለዋል። አሁን ባለው አሰራር ተማሪዎች ወደ መሰናዶ ትምህርት ሲገቡ ቢፈልጉም ባይፈለጉም 70 በመቶ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ 30 በመቶ በማህበራዊ ሳይንስ የሚመደቡ መሆኑን አስታውሰው ለተማሪዎች ውጤታማነት ሲባል አሰራሩ እንደገና እንደሚታይ ጠቁመዋል። የሀገሪቱን የሰው ኃይል ፍላጎት መሰረት አድርጎ ተማሪዎች የሚፈልጉትን ትምህርት እንዲያጠኑ የሚያደርግ አሰራር ይካተትበታል ብለዋል። በፍላጎትና በአቅርቦት የተሟላ ትምህርት በማቅረብ ኢኮኖሚውን ከግብርና መር ወደ ኢንዱሰትሪ መር ለማሸጋገር ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት እንደሚያግዝም ተናግረዋል። ፍኖተ ካርታው ከዚህ በፊት የነበረውን የትምህርት መዋቀር የሚያሻሽልና ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው። በዚህም ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት፣ ከ7ኛ እስከ 8ኛ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት፣ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተብሎ ጎን ለጎን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የሚሰጥበት መርሃ ግብር ይሆናል።   የትምህርት ሚኒስቴርንም የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ሚኒስቴር፣ አጠቃላይ የትምህርትና ስልጠና ሚኒስቴር እና  የክህሎትና ሥራ ፈጠራ ሚኒስቴር ተብለው በሶሰት እንዲዋቀሩ የሚያደርግ ነው።   በፌዴራል ደረጃ ውይይት እየተደረገበት ሲሆን ወደ ክልል ወርዶ ውይይት እንደሚደረግበትም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም