ቀጥታ፡

ሀገር ለማፍረስ የመጣውን የአሸባሪ ቡድን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ዘመቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነትን" እየመሩት ነው

ህዳር 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሀገር ለማፍረስ የመጣውን አሸባሪው ህወሃትን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ "ዘመቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነትን " እየመሩት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታወቀ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሸባሪው ህወሃት በህዝብ ትግል ከተወገደበት ስልጣን ለመመለስ ጦርነት መጀመሩን አስታውሰው "ለአለማቀፉ ማህበረሰብ ግን ለትግራይ ህዝብ እንደሚታገሉ አድርጎ ፕሮፓጋንዳቸውን ያቀርባሉ" ብለዋል።

“ኢትዮጵያ በመፍረስ ላይ ናት” ብለው አንዳንድ አካላት ድብቅ አላማቸውን ለማሳካት የፈጠራ ወሬ እንደሚያሰራጩ ገልጸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና መንግስታቸው ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ያለውን አለመግባባት በሰላም ለመፍታት ባለፉት ሶስት አመታት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በትግራይ ክልል የሚቀርበው የሰብአዊ ድጋፍ 70 በመቶውን መንግስት እየሸፈነ መሆኑንና ለክልሉ ህዝብ ተጠቃሚነት የተናጠል ተኩስ ማቆም ቢያደርግም አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልል አካባቢዎች ወረራ መፈጸሙን ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት በትግራይ ክልል የርሃብ ችግር እንዳለ በማስመሰል የሰብአዊ ድጋፉን አለም አቀፍ አጀንዳና ፖለቲካዊ በማድረግ ወደ ስልጣን ለመመለስ እየተጠቀመበት ይገኛልም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰላም ግንባታ ረገድ የተለያዩ ተግባራዊ ስራዎችን ማከናወናቸውን ያስታወቁት ኃላፊዋ፤ አሸባሪው ህወሃት ግን በሚነዛው ውሸት እውነታውን እንዳዛባው አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላምን ለማረጋገጥ የተሻሉ መንገዶችን እንደሚጠቀሙና ማንም ከኢትዮጵያውያን በላይ ለኢትዮጵያ ሊያስብ እንደማይችል አመልክተው፤ “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመቻውን መምራት የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር ያለመ ነው” ብለዋል።

“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደ ኢትዮጵያ መሪና የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥነታቸው ሀገርን ለማፍረስ የመጣውን ቡድን በህግ ተጠያቂነቱን ማረጋገጥ አለባቸው፣ በዚህም "ዘመቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" ን እየመሩት ነው ሲሉ” አስታውቀዋል።

አለም አቀፉ ማህበረሰብም ሕጋዊ ከሆነው የኢትዮጵያ መንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባ አስገንዝበው ኢትዮጵያ ይህን ወቅት በማለፍ ወደ ልማት የምታደርገውን ጉዞ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም