ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ህልውና መጠበቅ ያሳዩት ጀግንነት ኢትዮጵያን ለመንካት የሚሹ አካላት ደጋግመው እንዲያስቡ ትምህርት የሚሰጥ ነው

አዲስ አበባ ህዳር 27/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ህልውና መጠበቅ ያሳዩት ጀግንነት ኢትዮጵያን ለመንካት የሚሹ አካላት ደጋግመው እንዲያስቡ ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሠራተኞች ገለጹ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች በአፋር ክልል በመገኘት ለመከላከያ ሰራዊትና በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አድርገዋል።   

ሰራተኞቹ ለመከላከያ ሰራዊት ደም ለግሰዋል፤ የአንድ ወር ደሞዛቸውን እንዲሁም በአሸባሪው ሕወሃት ለተፈናቀሉ ዜጎችም ምግብ ነክ ቁሳቁሶች ድጋፍም አድርገዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ህልውናዋና ሉዓላዊነቷ የተከበረ ኢትዮጵያን ለቀጣይ ትውልድ የማሻገር ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን መደገፍ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ኢንስቲትዩቱ ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች የህልውና ዘመቻው ከተጀመረ አንስቶ ለመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ህልውና መጠበቅ ያሳዩት ጀግንነት ኢትዮጵያን ለመንካት የሚሹ አካላት ደጋግመው እንዲያስቡ ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲሉም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

የኢንስቲትዩቱ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግርማ ደጀኔ በበኩላቸው የኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች ለህልውና ዘመቻው ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውንና ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም  ነው የገለጹት፡፡

ከዚህ በኋላ በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችን በሁሉም መስክ መልሶ ማቋቋም የሁላችንም ቀጣይ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ይሽሩን ዓለምአየሁ ናቸው።

ሌላው የተቋሙ ሰራተኛ ዶክተር ሰብሉ ሁምኔ በበኩላቸው አንድነታችንን አጠናክረን ከመንግሥት ጎን በመሆን አሸናፊነታችንን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ተወካይ ብርጋዴል ጀነራል ተመስገን አቦሴ "ለኢትዮጵያ ህዝብ አንዴ አይደለም ሁለቴ ሦስቴም ብንሞት የሚቆጭ አይደለም፤ በጋራ በመሆን ጁንታውን ፍጻሜ እናፋጥናለን ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም