ቀጥታ፡

ደርጅቱ ለመከላከያ ሰራዊት ከ2ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሶችን አበረከተ

ደብረብርሀን ህዳር 27/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ እንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ደርጅት በግንባር ከጠላት ጋር እየተፋለመ ላለው የሀገር መከላከያ ሰረዊት ከሁለት ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሶችን አበረከተ።
የድርጀቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ የሺመቤት ነጋሽ በርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ወቅት፤  የታሪካዊ ጠላቶቻችን ተላላኪ የሆነውን የአሸባሪው ህወሃትን ሴራን ለማክሸፍ የመከላከያ ሰራዊቱና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች  መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ናቸው ብለዋል።

የሚከፍሉት ዋጋም አሸባሪው ቡድን በደረሰባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ንጹሃንን በመግደል፣ የመንግስትና የግል ሃብትን በመዝረፍና ንጹሃንን በማፈናቀል የፈጸመውን የጥፋት ጥግ ለመግታት መሆኑን ገልጸዋል።

ቡድኑ በወረራቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚገኙ የድርጅቱ 12 ቅርጫፍ የሽያጭ ማዕከላት ውስጥ የነበረ 500 ሚሊየን ብር የሚገመት ሀብት በመዝረፍና በማውደም  ጥፋት መፈጸሙንም ጠቁመዋል።

አሁን ላይ በሃገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች የጀግንነት ተጋድሎ ነፃ በወጡ አካባቢዎች  ስራውም ለማስቀጠል እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

ድሉን እያስመዘገበ ለሚገኘው ሰራዊትም የደርጅቱ ሰራተኞች ከወር ደመወዛቸው  በማዋጣት ሁለት ሚሊየን ብር የሚገመቱ ቁሶች  ድጋፍ በደብረ ብርሃን ከተማ በመገኘት አበርክተዋል።

ከድጋፉም   ውስጥ 100 ፍራሽና 100 አንሶላ፣  229ሺህ እሽግ ጁስ፣  2ሺህ ካርቶን ብስኩት፣ 250 እሽግ ውና 26ኩንታል በሶና 20 ኩንታል ስኳር እንደሚገኝበት አመልክተዋል።

ድጋፉን ከተረከቡት መካከል ሜጀር ጀነራል ሐብታሙ ጥላሁን በበኩላቸው፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እያደረገ ያለው ድጋፍ ለመከላከያ ሰራዊቱ ጽናትና ቁርጠኝነትን የሚያላብስ ነው ብለዋል።

በተለይም አሁን ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአካል በጦር ሜዳ ተገኝተው ሰራዊቱን በመምራት እያስመዘገቡት ያለው ድል የውጪና የውስጥ ጠላቶቻችን ሽንፈት ያከናነበ መሆኑ ተነሳሽነትን እንደሚጨምር ማድረጉን ነው ያመለከቱት።

ይህም እንደ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ያሉ ተቋማትና መላ ህዝቡም የገንዘብና ዓይነት   ድጋፍ በማድረግ የደጀንነት ሚናውን መወጣታቸውም እንዲሁ።

በተለይም ድርጅቱ ያደረገው ድጋፍ  ለሰራዊቱ አባላት የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ አመስግነዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ በተካሄደው የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የፌደራልና የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም