የቻይና-አፍሪካ የሶስት አመት ርዕይ

33

የቻይና-አፍሪካ  ወዳጅነት በእኩልነትና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን ዋና መርህ አድርገው የጋራ ጉዞ ማድረግን መርጠዋል። ቻይና በአገራት መካከል ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስፈለገው ሴራ ሳይሆን በእኩልነት ላይ የተመሰረት ትብብርና በጋራ ጥቅም ላይ በመመስረት ጠንክሮ መስራት ነው የሚል እምነት የያዘችና በተግባር እያሳች ያለች አገር ናት፡፡

በሰሞኑ ይህኑን የሚያጠናክር ሃሳብ በ8ኛው የቻይና-አፍሪካ ወዳጅነት የሚኒስትሮች ጉባኤ በሴኔጋል ዳካር በተካሄደበት ወቅት ተሰምቷል፡፡ 

በዚሁም ወቅት የቻይና-አፍሪካ ወዳጅነት እና ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በዌቢናር ባስተላለፉት መልዕክታቸው ማስታወቃቸውም የሚታወስ ነው፡፡

በዚሁ ጉባኤ ላይ ትኩረት ያገኘው ጉዳይ ቻይና ከአፍሪካ ድህነትን ለመቀነስ እና በግብርናው ዘርፍ ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ 10 ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ወደ ተግባር ለማስገባት መዘጋጀቷን ማሳወቅ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪም በንግድ፣ በታዳሽ ኃይል እና በክትባት አቅርቦት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጣለች፡፡

ይህ የቻይና ውሳኔ ደግሞ ለአህጉረ አፍሪካ ያለው በረከት በብዙ መልኩ የሚታይ ነው። በተለይም የማደግ ችግር ለሚፈታተነው የወጪ ንግድ ትልቅ ተስፋ ይሆናል። አብዛኛው የወጪ ንግድ የሚመነጨው ከግብርና ምርት መሆኑ ደግሞ የችግሩን ትክክለኛ ቦታ እንደተመለከተ መረዳት ይቻላል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያም የጎላ ተጠቃሚነት እንደሚኖራት ይጠበቃል።

በተለይ ከአሜሪካ ከቀረጥ ነፃ እድል (አጎዋ) የታጣውን ዕድል በተሻለ መልኩ ለማካካስ የሚያስችል ይሆናል፡፡ የአፍሪካን የወጪ ንግድ ለማገዝ ቻይና 10 ቢሊዮን ዶላር እንደምታቀርብ የቻይና ፕሬዚደንት ሺ ዢንፒንግ አረጋግጠዋል፡፡

‘ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሺየቲቭ’ በተባለው የቻይና ዕቅድ ላይ በሚመረኮዘው መርሐ-ግብር አገራቸው የአፍሪካ አገሮችን እርስ በርስ የሚያገናኙ አስር የመሠረተ-ልማት ግንባታዎች ለማከናወን እና ከአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ጽህፈት ቤት ጋር የኢኮኖሚ ትብብር የሚያስተባበሩ የባለሙያዎች ቡድን ለማቋቋም ሺ ዢንፒንግ ቃል ገብተዋል።

ሌላኛው በኢኮኖሚው ዘረፍ የተቀመጠው ርዕይ አስር የኢንዱስትሪ ማስፋፊያ እና የሥራ ፈጠራ ፕሮጀክቶችን እውን እንዲሆን የቻይና ኩባንያዎች ከ10 ቢሊዮን ዶላር የማያንስ መዋዕለ-ንዋይ በአፍሪካ እንዲያፈሱና የቻይና አፍሪካ የግል መዋዕለ ንዋይ መድረክ ማቋቋም  ነው። 

በተጨማሪም ቻይና እስከ 2024 ዓ.ም ድረስ እስከ 300 ቢሊዮን ዶላር የአፍሪካን ቁሳቁሶች ከአፍሪካ አገሮች  መሸመት ትፈልጋለች። ይህም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች፤ ለሌሎች ትልልቅ የግብርና አምራች አገሮች በጣም ሊጠቀሙ የሚያስችል ነው፡፡

ከግብርናው ዘርፍ በተጨማሪም ቻይና በአፍሪካ አስር የዲጂታል ኤኮኖሚ ፕሮጀክቶች መገንባት፤ በሳተላይት እና በኤሌክትሮኒክ ግብይት ዘርፎች ትብብሮችን ማጠናከር፣ አስር የአረንጓዴ ልማት እና የከባቢ አየር ጥበቃ ፕሮጀክቶች፣ አስር ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እና ለማደስ፣ 10 ሺህ የአፍሪካ ከፍተኛ ባለሙያዎችን በአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እና ስብሰባዎች ለመጋበዝ ርዕይ አስቀምጣለች።

ይህ ርዕይ በእኩልነትና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን መሰረት ያደረገ ትብብር ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በ2035 ለማሳካት የታቀዱ ዘጠኝ ተግባርም ተለይተዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው የአፍሪካና የቻይና ወዳጅነት ዘላቂነት ያለው የረጅም ጊዜ በግልጽ፣ በሚለካና በሚሰፈር ርዕይ ላይ የተመሰረተ ለአህጉሪቱ ብልጽግና ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ፕሮጀክት መሆኑን የሚያመላክት ሲሆን አፍሪካዊያንም በወንድማማችነት መንፈስ አንድነታቸውን አጠናክረው ዕድሉን በአግባቡ ሊጠቀሙበት የሚገባ ነው፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም