በሉዓላዊነታችን ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት በአንድነት ተነስተናል - ወጣቶች

ጎባ፤ ህዳር 26/2014 (ኢዜአ) በሉዓላዊነታችን ላይ የተቃጣውን ጥቃት ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ለመመከት በአንድነት ተነስተናል ይላሉ የባሌ ዞን ወጣቶች።

ወጣቶቹ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሀገርን ለማዳን  ግንባር ድረስ ዘምተው ሰራዊቱን በመምራት በጠላት ላይ እየተቀዳጁ ያሉት አኩሪ ድል መከላከያን ለመቀላቀል ይበልጥ አነሳስቷቸዋል።

ወጣት አበረ ገመቹ እንዳለው  የሀገር ሉአላዊነት ዓርማ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት ለመቀላቀል ተዘጋጅቷል።

“በሀገር ላይ የተቃጣውን የውስጥና የውጭ ትንኮሳ በመመከት ሉዓላዊት ኢትዮጵያ እንድትቀጥል የሚጠበቅብኝን የዜግነት ኃላፊነት ለመወጣት ተነሳስቼያለሁ" ብሏል፡፡

“ጀግኖች አባቶች በከፈሉት መስዋዕትነት ለዛሬ የበቃችው ሉዓላዊት ኢትዮጵያ በውስጥና ውጭ ጠላቶች እንዳትደፈር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሴን አሻራ ለማኖር መከላከያን ለመቀላቀል ወስኛለሁ” ያለው ደግሞ ወጣት ከድር መሐመድ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ጥቃት ለመመከት በአንድነት ልንነሳ ይገባል”  ያለው ወጣቱ፤ እሱም ሌሎችንም በማስተባበር  አካባቢው ከጥፋት ተላላኪዎች ከመጠበቅ ባለፈ ወደ ግንባር ለመዝመት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሀገርን እየፈጸመ ያለውን ጥቃት ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ  ለመመከት በአንድነት መነሳታቸውን ነው ወጣቶች የገለጹት።

የባሌ ዞን  ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው “የዞኑ ወጣቶች ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊትን በፍላጎታቸው ለመቀላቀል የወሰኑት ውሳኔ የሚያኮራና ታሪካዊ ነው” ይላሉ።

ወጣቶቹ የሀገሪቱን አንድነትና ሉአላዊነት ለማስከበር በግንባር ለተሰለፈው የመከላከያ ሰራዊት የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በባሌ ዞን የተገኙት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የመንግስት ኃብት አስተዳዳር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በሰጡት አስተያየት፤ በእነጀነራል ዋቆ ጉቱና መሰል ጀግኖች አካባቢ  ተገኝቼ ለሀገር ሉዓላዊነት ቅድሚያ የሰጡ ወጣቶችን ስመለከት ደስታ ይሰማኛል ነው ያሉት፡፡

የባሌ ህዝብ ጭቆናን የማይቀበልና ለመብቱ የሚታገል ማህበረሰብ መሆኑ ታሪክ እንደሚመሰክር ያወሱት ዶክተር ግርማ፤ "የዛሬ ወጣቶችም የጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪን ተከትላችሁ መከላከያን ለመቀላቀል መወሰናችሁ ለሀገር አንድነት ያላችሁን ቀናኢነትና ክብር የሚያሳይ ነው" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም