ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል የሰው ኃይልና የገንዘብ እጥረት መኖሩ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል የሰው ኃይልና የገንዘብ እጥረት መኖሩ ተገለጸ
አዲስ አበባ ነሀሴ 17/2010 በኢትዮጵያ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የገንዘብ እጥረት መኖሩን የግብርናና እንስሳት ኃብት ሚኒስቴር አስታወቀ። ችግሩን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ብሏል። ሚኒስቴሩ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር አንድ ጤና በሚል መሪ ቃል በሽታዎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የግንዛቤ ማስጨበጫ አውደ ጥናት እያካሄደ ይገኛል። የሰውን ልጅ ከሚያጠቁ በሽታዎች መካከል በአማካይ 75 በመቶ የሚሆኑት ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይ የአባሰንጋ በሽታ ከእንስሳት ወደ ሰው ከሚተላለፉ በሽታዎች ውስጥ ቀዳሚ ሲሆን ለበርካታ እንስሳትና ሰው ሞት ምክንያት እየሆነ ይገኛል። በግብርናና እንስሳት ኃብት ሚኒስቴር ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ባለሙያ ዶክተር አክሊሉ ተስፋዬ እንደገለጹት የአባሰንጋ በሽታ በአብዛኛው ደረቅና ሞቃታማ የአየር ንብረት ባለበት አካባቢ የሚከሰት ነው። በሽታው የሚተላለፈው በጥሬ ስጋና ባልፈላ ወተት እንዲሁም በበሽታው ከተያዘ እንስሳት በሚወጣ ትንፋሽ አማካይነት ነው። በአገሪቱ የእንስሳት ጤና አገልግሎትን የተጠናከረና የተሟላ ለማድረግ ዘርፉ በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ የገንዘብና የመድሃኒት አቅርቦት ችግር ማነቆ እንደሆነ ገልጸዋል። የእንስሳት ጤና አገልግሎትን በማሳደግ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን በመከላከል በኩል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የበሽታ ስርጭት ቁጥጥር መምህር ዶክተር በሪሁን አፈራ እንዳሉት የአባሰንጋ በሽታ ትኩረት ያልተሰጠው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ኅብረተሰቡ ተጠቂ እንዳይሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በስፋት ማከናወን ያስፈልጋል። በደቡብ ክልል እንስሳትና ዓሳ ኃብት ቢሮ የእንስሳት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ አለማየሁ በበኩላቸው በሽታውን ለመከላከል እንስሳትን በተለያዩ ጊዜያት ወደ ህክምና ተቋም በመውሰድ ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2014፣ 2015 እና በ2016 በኢትዮጵያ በተደረገ ጥናት የአባሰንጋ በሽታ በብዛት ከሚከሰትባቸው አካባቢዎች መካከል የአማራ፣ የትግራይና የደቡብ ክልሎች ቀዳሚ ናቸው። በተመሳሳይ በ1999 እና በ2000 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተደረገ ጥናት 1 ሺህ 600 የዱር እንስሳት በአባሰንጋ በሽታ ሞተዋል።