በመድሃኒት አጠቃቀም ዙሪያ ማህበረሰቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው የፋርማሲ ባለሙያዎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በመድሃኒት አጠቃቀም ዙሪያ ማህበረሰቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው የፋርማሲ ባለሙያዎች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።

''ፋርማሲስቶች የመድሃኒትዎ ሊቃውንት እና የጤና አገልግሎት የፊት መስመር ተሰላፊዎች'' በሚል መሪ ሃሳብ ስምንተኛው የኢትዮጵያ የፋርማሲስቶች ቀን ዛሬ ተከብሯል።

በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት ጄነራል ዳይሬክተር ዶክተር ህሊና ታደሰ፤ በእለቱ ባደረጉት ንግግር የፋርማሲ ባለሙያዎች ለታካሚዎች የሚታዘዙ መድሃኒቶችን አጠቃቀምና የጎንዮሽ ጉዳት በተመለከተ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ላይ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።

"የፋርማሲ ባለሙያዎች የመድሃኒት ሊቃውንት" እንደመሆናቸው መጠን ህብረተሰቡን በዛው ልክ በማስረዳት ግንዛቤ በመፍጠር ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

መድሃኒቶች ወደ ማህበረሰቡ  ደርሰው በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋሉ  የሰው ልጅ ህይወትን እንደሚታደጉ ሁሉ  በአጠቃቀም ችግር ደግሞ ለከፍተኛ የጤና ቀውስ ብሎም ለሞት ሊዳርጉ ይችላሉ ሲሉም አስረድተዋል።

በጤና ሚኒስቴር በኩል በመድሃኒት አቅርቦትና ተደራሽነት እንዲሁም ባለሙያዎች ለታካሚዎች እየሰጡ ባለው አገልግሎት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም በችግሩ ስፋት ልክ አልተሰራም ያሉት ዶክተር ህሊና በቀጣይ በጤናው ዘርፍ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር የተሻለ ክንውን ይኖራል ብለዋል።

ለዚህም ስኬት የፋርማሲ ባለሙያዎችና ማህበሩ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቅስው በጤናው ዘርፍ የገጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ይበልጥ ተቀራርቦ መስራት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ ሰይፋ በበኩላቸው፤ አግባብነት ያለው የመድሃኒት አጠቃቀም በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበሩ ከጤና ሚኒስቴርና የተለያዩ የጤና ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም