በአዲስ አበባና ሌሎችም አካባቢዎች ተዘዋውረን ያለምንም ስጋት እየጎበኘን ነው፤ ዜጎቻቸው እንዲወጡ የሚወተውቱ አገሮች አስገርመውናል

22

አዲስ አበባ፤ ህዳር 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባና ሌሎችም አካባቢዎች ተዘዋውረን ያለምንም ስጋት እየጎበኘን ነው፤ ዜጎቻቸው እንዲወጡ የሚወተውቱ አንዳንድ አገሮች ግን አስገርመውናል ሲሉ በጉብኝት ላይ ያሉ የውጭ አገር ዜጎች ተናገሩ።

ማርኮ ዳጋስፐር እና ማርክ ቻፕማን ኑሯችውን በአዲስ አበባ ካደረጉ የውጭ አገራት ዜጎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በቱሪዝም አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩት ሁለቱ ጓደኛሞች በአስጎብኚ ድርጅታቸው በኩል ደንበኞቻቸውን እየያዙ በቱሪዝም መዳረሻዎች እየተዘዋወሩ በመጎብኘት ላይ ናቸው።

አዲስ አበባ አሁንም በነፋሻማዋ አየር የነፍስ ሃሴት የሚገበይባት፤ በሰላም ወጥተው አሻቸው ስፍራ ደርሰው የሚመጡባት ፍፁም ሰላማዊ ከተማ መሆኗንም ይናገራሉ።

ሰሞኑንም ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በ135 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ወንጪ ሃይቅ ሲጎበኙ አግኝተናቸዋል።

"ኢትዮጵያ የምወዳት ውብ ሀገር ነች፤ ባለፈው ሳምንት በአንኮበር እና በወልቂጤ ጉብኝት አድርጌያለሁኝ ሁሉም አካባቢ በጣም ሰላም ነው፤ ዛሬ ደግሞ ወንጪ እገኛለሁ፤ በተመለከትኩት ሁሉ ደስተኛ ነኝ" ይላል ማርክ ቻፕማን።

እውነታው ይህ ሆኖ እያለ አንዳንድ የምእራቡ ዓለም ሚዲያዎች በአዲስ አበባና አካባቢው ሰላም እንደሌለና የጦርነት ቀጠና በማስመሰል በሚያሰራጩት የተሳሳተ መረጃ መገረሙን ገልጿል።

አዲስ አበባ ፍፁም ሰላማዊ ከተማ ነች፤ አንዳንድ አገሮች ግን ዜጎቻቸው እንዲወጡ ሲወተውቱ እንሰማለን፣ በዚህም ተገርመናል" ብለዋል ማርኮ ዳጋስፐር እና ማርክ ቻፕማን።

በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚሰማው ጦርነት በስተቀር በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ምንም አይነት ስጋት የለም እንደ ልብ መንቀሳቀስ ይቻላል ሲሉም ይናገራሉ።

በአዲስ አበባና ሌሎችም አካባቢዎች ተዘዋውረን ያለምንም ስጋት እየጎበኘን ነው፤ ዜጎቻቸው እንዲወጡ የሚወተውቱ አንዳንድ አገሮች ግን አስገርመውናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሰፊ አገር ነች፤ ወደ ሰሜን ጉዞ ማድረግ ባይቻልም በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች ግን ፍፁም ሰላማዊ ነው፤ ማንም ሰው መንቀሳቀስና መጎብኘት ይችላል ሲሉም ይናገራሉ።

ኢትዮጵያን መጎብኘት የሚሹ የውጭ ዜጎች በርካታና ድንቅ የሆኑ ተፈጥራዊና ሰው ሰራሽ መስህቦቿን በነፃነት ተዘዋውረው መመልከት ይችላሉ ብለዋል።

በተለይም የ2021 የዓለም ተመራጩ የኢኮ ቱሪዝም መንደር በሚል በዓለም ቱሪዝም ድርጅት የተመረጠው ወንጪ ሐይቅ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ያለ ማራኪ መዳረሻ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፤ በቱሪዝም ጸጋዎች የታደለችው ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ አምስት የቱሪስት ኮሪደሮች እንዳሏት ያብራራሉ።

በመሆኑም አሁን ላይ ከሰሜን ኢትዮጵያ በስተቀር አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች ባሉ የቱሪስት መዳረሻዎች ያለምንም ስጋት ተዘዋውሮ መጎብኘት ይቻላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም