አሸባሪው የህወሃት ቡድን በጋሸና አካባቢ በቆየባቸው ጊዜያት ከፍተኛ ግፍና በደል ፈፅሞብናል

70

ደብረ ታቦር፤ ህዳር 25/2014(ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ወራሪ ቡድን በጋሸና አካባቢ በቆየባቸው ጊዜያት እያስፈራራ በማስጨነቅ ከፍተኛ ግፍና በደል ፈፅሞብናል ይላሉ የጋሸና ከተማ ነዋሪዎች።

ነዋሪዎቹ በሰራዊቱ ተጋድሎ ከአሸባሪው ጭቆና ነጻ በመውጣታቸው የተሰማቸውን ደስታም እየገለጹ ነው።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል  ቄስ በሪሁን ከበደ፤ የአሸባሪው ቡድን አባላት  ሰው ሆኖ ከተፈጠረ የማይጠበቅ ዘግናኝ ግፍ፣ መከራና ስቃይ ፈጽመውብናል ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።

''እኛ ጠባችንና ጠላታችን ከብልጽግና አመራሮች እንጂ ከህብረተሰቡ አይደለም'' እያሉ አታለው ወደ ከተማው ከገቡ በኋላ ህጻናትን ሳይቀር መግደላቸውን፤ መድፈራቸውንና ንብረት መዝረፋቸውን ይገልጻሉ፡፡

''የሌለንን የጦር መሳሪያ ደብቃችኋል፤ ጉድጓድ ውስጥ ቀብራችኋል አምጡ'' በማለት ጠብመንጃ  ግንባራቸው ላይ በመደቀን ሲያስጨንቋቸው እንደቆዩ ቄስ በሪሁን አስታውሰዋል።

አሁን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መሪነት በተጀመረው ማጥቃት ከፍተኛ ምት ደርሶባቸው ሲፈረጥጡ ከጥፋታቸው አልማር ብለው ተጨማሪ ጥፋት እያደረሱ በዱር በገደሉ መግባታቸውን  ጠቁመዋል።

በሰራዊቱ እልህ አስጨራሽ ትግል ከአራት ወራት ጭቆና ተላቀን ነጻ በመውጣታችን በእጅጉ ተደስተናል ብለዋል  ቄስ በሪሁን።

ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ መሬም መሃመድ፤  የሽብር ቡድኑ ለአቅመ ደካማና ለድሃ እንኳ የማያዝን ክፉ መሆኑን ነው የተናገሩት።

'' አቅመ ደካማ በመሆኔ አስፓልት መንገድ ዳር ሻይ ቡና እየሸጥሁ ቤተሰቤን ሳስተዳድር ብቆይም በሽብር ቡድኑ ምክንያት ስራ አቁሜ ለችግር ተዳርጌ ቆይቻለሁ '' ብለዋል፡፡

''አሁን ከተማችን ነፃ በመውጣቷ ስራ ጀምሬ ወደ ቀድሞ ህይወቴ ለመመለስ እየሞከርኩ ነው'' ያሉት ወይዘሮ  መሬም፤ ለቀጣይ ድል ሰራዊቱን በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የህውሃት ወራሪና ዘራፊ ቡድን በመሬት ላይ እንዲኖር መፍቀድ ተጨማሪ ግፍ እንዲፈፅም እድል መስጠት በመሆኑ አሁን በተጀመረው አግባብ  የጥፋት ሴራውን ማክሸፍ  እንደሚገባም አመልክተዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ተመስገን ቢረሳው በበኩላቸው፤ የሽብር ቡድኑ በህዝብ ላይ ግፍና ሰቆቃ በመፈጸም አረመኔነቱንና አውሬነቱን በተግባር አረጋግጧል ብለዋል፡፡

እድሜ ልኩን የኢትዮጵያን ህዝብ መዝረፉ፣ መግረፉና መግደሉ ሳይበቃው  አሁንም  ሀገርን  ለመበታተን ቢጥርም የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ እየመከተው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ ጋሸና ላይ ያለ የሌለ አቅሙን ተጠቅሞ የሰራው ምሽግም በቅንጅት ተሰብሮ  ለከፍተኛ ኪሳራ በመዳረጉ  ከሞት የተረፈ ኃይሉ እግሩ እንደመራው እየፈረጠጠ ነው ብለዋል፡፡

በሽብር ቡድኑ ተወረው የነበሩ የዞኑ አካባቢዎችም ነጻ እየወጡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለማምለጥ  የሚሞክሩ የአሸባሪው ርዝራዦች  ህዝቡ ተከታትሎ በመቆጣጠር  መሳሪያቸውን መታጠቅና አካባቢውን መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም