በጦርነቱ ሳቢያ ሊከሰት የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም የመስኖ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው

62

ህዳር 24/2014/ኢዜአ/ በጦርነቱ ሳቢያ ሊከሰት የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም የመስኖ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሣ ተናገሩ።

በተያዘው የበጋ ወራት ባለፈው ዓመት በዘር ከተሸፈነው መሬት በእጥፍ የማሳደግ ዕቅድ መያዙንም ገልጸዋል።

በክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሣ፤ የተመራ ልዑክ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን እና በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን በበጋ መስኖ እየለማ የሚገኝን የስንዴ ክላስተር ጎብኝቷል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት አቶ ሽመልስ አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ እንዲጠፉ ህዝቡ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ እና ልጆቹን ወደ ጦር ግንባር በመላክ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በኢኮኖሚው ግንባርም አርሶ አደሩ የአገር ዋልታነቱን ዳግም ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክሮ በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።  

በጦርነቱ ሳቢያ ሊከሰት የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና ለማካካስ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከምን ጊዜውም በላይ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

የደረሱ ሰብሎችን በአፋጣኝ በመሰብሰብ በበጋ የመስኖ ስንዴ የማልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት 607 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መገባቱንም ተናግረዋል፡፡

የመስኖ ስራው በሁለት ዙር እንደሚከናወን ጠቅሰው በአንደኛው ዙር 350 ሺህ ሄክታር መሬት ይሸፈናል ያሉት ፕሬዝዳንቱ እስከአሁን 82 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑንም ጠቁመዋል፡፡

በክረምቱ ወራት በክልሉ በተሰራው የስንዴ ልማት እና በበጋ ወራት በሚሰራው የመስኖ ልማት ከውጭ አገር የሚገባውን የስንዴ ምርት ማስቀረት ያስችላል ነው ያሉት።

በዚህም በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን የውጭ ጫና መቀነስ እንችላለን ብለዋል፡፡   

በተያዘው በጀት ዓመት 20 ሺህ የውሃ ፓምፖችን ከውጭ በማስገባት ለአርሶ አደሮች ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግስት በኩል አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የገለጹት አርሶ አደሮችም በመስኖ ስንዴን ማልማት ከጀመርን ወዲህ ተጠቃሚ ሆነናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም