በተሸከርካሪ አደጋ የሰድስት ሰዎች ህይወት አለፈ

60

ጎንደር ፤ ህዳር 24/2014 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ ወለቃ አካባቢ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የስድስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ዛሬ  ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ የተከሰተው አደጋ ከሁመራ ወደ ጎንደር ሰሊጥ ጭኖ ሲጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-41239 ኢት ሲኖ ትራክ ባለ ተሳቢ ከባድ የጭነት ተሸከርካሪ መንገድ ስቶ በመገልበጡ ነው።  

በአደጋው አሽከርካሪውን ጨምሮ በተሽከርካሪው ላይ  የተሳፈሩ  አንድ ወንድና አንዲት ሴት ከህጻን ልጇ ጋር እንዲሁም በመንገድ ላይ ሲጓዙ የነበሩ ሁለት ሰዎች  ህይወታቸው ወዲያውኑ ማለፉን ፖሊስ አስታውቋል።

የከተማው ፖሊስ መምሪያ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር እየሩስ አስማረ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በተጨማሪም ሁለት እግረኞች የአካል ጉዳት ደርሶባቸው  በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡

የአደጋውን መንስኤ ፖሊስ እያጣራ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሽከርካሪዎች  ተጠንቅቀው ሊያሽከረክሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም