የተደራጁ የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው

46

ህዳር 24/2014/ኢዜአ/ የተደራጁ የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል ከመደበኛው ቁጥጥር ባሻገር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።

የባንኩ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ለኢዜአ እንዳሉት የሕግ ማስከበር ዘመቻውን ተገን በማድረግ የሚሰሩ ኢኮኖሚያዊ ወንጀሎችን ለመከላከል ጥብቅ  ቁጥጥር እየተደረገ ነው።

ባንኩ ከመደበኛ የቁጥጥር ተግባሩ ባሻገር ከመረጃና ደህንነት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከጸጥታ አካላትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ባንኮች ለተለያዩ ወንጀሎች እንዳይጋለጡና ኢኮኖሚው በአሻጥር አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ከሁሉም ባንኮች አመራሮች ጋር ስምምነት ላይ ተደርሶ ወደ ስራ እንደተገባም ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ይናገር ገለጻ ለወንጀል ተግባር የሚውል ገንዘብ በኢኮኖሚው ውስጥ እንዳይኖር ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው።

በዚህ አሰራር በኢኮኖሚው  ላይ የተደራጁ የፋይናንስ ወንጀሎችን ሲፈጽሙ በነበሩ ሰዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።

ቀደም ሲል በተወሰኑ ሴክተሮች ለተወሰነ ጊዜ የተወሰደው የባንክ ብድር እገዳ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚሰራውን ወንጀል ለመቆጣጠር ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህንና መሰል እርምጃዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ እንደሆነም አክለዋል።

ሁሉም ባንኮች ወንጀል እንዳይሰራ የተዘረጉ አሰራሮችን በጥብቅ ሥነ-ምግባር በመምራት የክትትል ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

ብሔራዊ ባንክ ኢኮኖሚው እንዲያገግምና ወደ ነበረበት እንዲመለስ የሚያደርገው ጥረት እና ኢኮኖሚው ላይ በሚሰሩ ወንጀሎች የሚወሰዱ እርምጃዎች ይቀጥላሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም