አሸባሪው ህወሃት በሴቶች ላይ የፈፀመው ድርጊት ፍጹም ከሰብአዊነት ያፈነገጠ ነው

74

ህዳር 24/2014/ኢዜአ/ አሸባሪው ህወሃት በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ በተለይም በሴቶች ላይ የፈፀመው ድርጊት ፍጹም ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ "የአውሬነት ተግባር ነው" ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ሴቶች ተናገሩ።

የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የህዝብ መገልገያ ተቋማትን፣ የግለሰብ ሃብትና ንብረትን በመዝረፍና በማውደም ፀረ- ህዝብ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።

በሸዋሮቢት እና ደብረ-ሲና ከተሞች በወረራ ገብቶ በነበረበት አጋጣሚ መድኃኒት ቤቶች፣ ባንኮች፣ ሆቴሎች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ የሸቀጣ-ሸቀጥ ሱቆችና ሌሎችንም ዘርፏል።

ከዘረፋው የተረፈውን ደግሞ በተለያየ መልኩ ከጥቅም ውጪ እንዲሆን በማድረግ በህዝብ ላይ የከፋ በደል ፈፅሟል።

የሽብር ቡድኑ በገባባቸው አካባቢዎች ወጣት ሴቶችን፣ እናቶችንና ህጻናትን ጭምር በመድፈር አሰቃቂ ወንጀል ፈፅሟል።

በጉዳዩ ላይ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ሴቶች፤ አሸባሪው ህወሃት በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ በተለይም በሴቶች ላይ የፈፀመው ድርጊት ፍጹም ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ "የአውሬነት ተግባር ነው" ብለዋል።

ወይዘሮ ኢትዮጵያ አስመሮም በሰጡት አስተያየት "የወለደች እናት እንዴት ትገደላለች? እንዴት ትደፈራለች? እንዴት ሳንጃ በአንጀቷ ይገባል? ይሄ ሰው ሳይሆን አውሬ ነው፤ አውሬም እኮ አይቶ ነው የሚበላው"

ወጣት ሳራ ሃይሌ በበኩሏ ንብረትን ከማውደም ባሻገር የሴት፣ የህጻናት፣ የወጣቶች፣ የነዋሪው አእምሮ እየተጎዳ ያለበትን ሁኔታ ተናግራለች።

"በዜጋው ላይ በእናቱ፣ በእህቱ፣ በወንድሙ ላይ ይሄንን ድርጊት ይፈጽማል ብዬ አላስብም።"ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ገነት አብርሃ ናቸው።

አንዳንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ጉዳይ ሃሰተኛ መረጃዎችን ከማሰራጨት ተቆጥበው በአሸባሪው ህወሃት እየተፈፀሙ ያሉ አሰቃቂ ወንጀሎችን ማጋለጥ አለባቸው ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ።

በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ምክንያት በተለይም በአማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ችግርና ሰብአዊ ቀውስ እየደረሰ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም