የሀዋሳ እና አርሲ ዩኒቨርሲቲዎች ለመከላከያ ሰራዊት ከ78 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ እና የአይነት ድጋፍ አደረጉ

75

ህዳር 24/2014 (ኢዜአ)የሀዋሳ እና አርሲ ዩኒቨርሲቲዎች ለመከላከያ ሰራዊት ከ78 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ እና የአይነት ድጋፍ አደረጉ።

ዩኒቨርሲቲዎቹ ጦር ሃይሎች በሚገኘው ምድር ሃይል ግቢ በመገኘት ድጋፉን አስረክበዋል።

የሀዋሳ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ እና የአርሲ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዱጉማ አዱኛ የዩኒቨርስቲያቸውን ድጋፍ አስረክበዋል።

የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብና ተማሪዎችን በማስተባበር ድጋፉ መሰባሰቡን ገልጸው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ የዘማች ቤተሰቦችን እየደገፉ እንደሚገኙና በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚንስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ ያለንበት ወቅት ኢትዮጵያዊነት እጅግ የደመቀበት ወቅት ነው ብለዋል።

ሁሉም በተሰማራበት መስክ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርጉ ስራዎችን ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል።

እየተደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ለሰራዊቱ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም